በኢቦላ ጊዜ በረራ የላቆመ አየር መንገድ ለኮሮና ቫይረስ አናቆምም ሲሉ አቶ ተወልደ...

በኢቦላ ጊዜ በረራ የላቆመ አየር መንገድ ለኮሮና ቫይረስ አናቆምም ሲሉ አቶ ተወልደ ተናገሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርጋቸውን በረራዎች፣ ቻይና ጊዜያዊ ችግር ባጋጠማት በዚህ ወቅት ማቋረጥ ተቀባይነት የለውም ሲሉ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገለጹ።

አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም “አየር መንገዱ ከ1973 ጀምሮ ወደ ቻይና በረራ ሲያደርግ ቆይቷል። አሁን ጊዜያዊ ችግር ስላጋጠማቸው ማቋረጥ በሞራልም በሥነ ምግባርም ተቀባይነት የለውም” በማለት  ከኢትዮጵያ ሕዝብ ደህንነት ይልቅ ከቻይናዊያን ጎን መቆም እንደሚያስፈልግ ያሳየ አስተያየት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርጋቸውን በረራዎች ቢያቆም የቻይናና የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ሙሉ ለሙሉ ይቋረጣል፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ያለ ማንም ሰው ይህ እንዲሆን እንደማይፈልግ እና ውሳኔው የአገሪቱ መሪዎችን ፍላጎት ጭምር መሆኑን አመልክተዋል።

ቻይና ከአፍሪካ ጋር ካላት ግኙነት አንጻር “ከአፍሪካዊያን እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ጎን መቆም አለብን”  ያሉት አቶ ተወልደ፤ የተከሰተውን የበሽታ ወረርሽኝ በመፍራት በርካታ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጓቸውን በረራዎች በማቋረጣቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስድ ግፊት እየተደረገበት ባለበት ጊዜ ነው ጠንከር ያለ ምላሽ የሰጡት።

በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን ችግር ለመከላከልም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፤ በረራዎችን ማቋረጥ ግን መፍትኄ ከሚሆኑ አማራጮች ውስጥ አይደለም ነው ያሉት ሓላፊው። አቶ ተወልደ እንዳሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርጋቸውን በረራዎች ቢያቆም መንገደኞች በሲንጋፖር በማሌዢያና በአውሮፓ በኩል ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን እንደማያቆሙ አመልክተዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራዎች ከበሽታው መከሰት ጋር በተያያዘ ያቋረጡ አየር መንገዶች የእራሳቸው ምክንያት እንዳላቸው ያመላከቱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ “የብሪቲሽ አየር መንገድ በረራውን እንዲቆም ያደረገው በእራሱ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ነው” ካሉ በኋላ ነገር ግን የቻይና አየር መንገዶች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በረራዎቻቸውን እያከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

“ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ ኢቦላ ከ8 ሺህ በላይ ሰዎችን መግደሉ አይዘነጋም። ነገር ግን በሽታው ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ እያለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደዚያው እየበረረ ነበር” ብለዋል አቶ ተወልደ።

ይህንን የተናገሩት አየር መንገዱን ለረጅም ጊዜ ላገለገሉ ሠራተኞች በተዘጋጀ የእውቅና ዝግጅት መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አምስት የቻይና ከተሞች በሳምንት 35 በረራዎችን በማድረግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መንገደኞችን ወደ አፍሪካ ያጓጉዛል።በዚህም ከአፍሪካ ወደ ቻይና በሚደረጉ በረራዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሚፎካከር አህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ የአየር ትራንስፖርት ሰጪ ተቋማት እንደሌሉ ተረጋግጧል።

LEAVE A REPLY