የጃዋር ጠባቂዎች ስራቸውን ለቀው ጃዋርን በግል መጠበቅ ጀምረዋል

የጃዋር ጠባቂዎች ስራቸውን ለቀው ጃዋርን በግል መጠበቅ ጀምረዋል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በመንግሥት ተመድበው ለረጅም ጊዜ ለጃዋር መሐመድ ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት በእራሳቸው ፈቃድ ከእርሱ ጋር ለመቆየት መወሰናቸው ተሰማ።

ከሳምንታት በፊት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ) በመቀላቀል ከመብት ተሟጋችነት ወደ ቀጥተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የገባው ጃዋር ሞሐመድ፤ ለቢቢሲ እንደተናገረው መንግሥት የመደባቸውን ጠባቂዎቹን እንደሚያነሳ ማሳወቁን ተከትሎ “ጠባቂዎቹ ከመደበኛ ሥራቸው ይልቅ እኔ ጋር መቅረትን መርጠዋል” ብሏል።

የኦሮሚያ ክልል የቴሌቪዥን ጣቢያ የፌደራል ፖሊስን ጠቅሶ ለጃዋር ሞሐመድ ተመድበው የነበሩት ጥበቃዎች እንዲነሱ መደረጉን ዘግቧል:: ጃዋርም በፌስቡክ ገጹ ላይ “ሰላም ነው። ከፌደራል ፖሊስ ጋር ተወያይተን ከስምምነት ላይ ደርሰናል፤ አታስቡ” ሲል ለደጋፊዎቹ መልዕክት ማስተላለፉ ይዘነጋም።

የጥበቃዎቹን መነሳት በተመለከተ ከፌደራል ፖሊስ ኮማንደር ጋር መነጋገሩን፣  አባላቱ ለስልጠና እንደሚፈለጉና ወደ ተቋማቸው እንዲመለሱ መጠየቁን ያልሸሸገው ጃዋር፤ ይህንን ተከትሎ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ጋር በተነጋገሩበት ወቅት የእሱ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ጥበቃ የተመደበላቸው ሰዎች ጠባቂዎችን ማንሳት እንደጀመሩና የእሱንም ጥበቃዎች እንደሚያነሱ እንደነገሩት ለቢቢሲ አረጋግጧል።

ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ ለረጅም ጊዜ አብረውት ከቆዩት ጠባቂዎቹ ጋር ስለዚሁ ጉዳይ ተነጋግሮ እንደነበር የሚናገረው ጃዋር “አነሱም ወደ ፌደራል ፖሊስ መመለስ እንደማይፈልጉና ከእኔ ጋር መቆየት እንደሚፈልጉ ነግረውኛል፤ ምክንያታቸውም ስምና ፎቷቸው በስፋት ሲሰራጭ ስለነበር ፣ ለደህንነታቸው በመስጋት እንደሆነ አስረድተውኛል” ያለው ጃዋር መሐመድ፤ ይህንን የጠባቂዎቹን ውሳኔ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ እንደተናገረና ኮሚሸነሩም የጠባቂዎቹ ፍላጎት ይህ ከሆነ ፣ የፖሊስ አባልነታቸውን በመተው  ከእሱ ጋር ሊቀጥሉ እንደሚገባ በመግለጻቸው፤ ” ጠባቂዎቹ በእጃቸው ላይ የነበረውን የጦር መሳሪያና የመንግሥት ንብረት መልሰው ከእኔ ጋር ቀርተዋል” ብሏል።

ለጃዋር ከፌደራል ፖሊስ ተመድበውለት ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩት የሠራዊቱ አባላት አራት ሲሆኑ ፣ አራቱም የፖሊስ አባልነታቸውን ትተው ከእሱ ጋር ለመሆን መወሰናቸውንም ተናግሯል።  የፌደራል ፖሊስ ቀደም ሲል ለተለያዩ ታዋቂ ፖለቲከኞች መድቧቸው የነበሩትን ጥበቃዎች የማንሳት እርምጃ እየወሰደ መሆኑ እንደተገለጸለት የሚናገረው ጃዋር “የእኔን ያንሱ ችግር የለብኝም፤ ብዙ ሕዝብ ነው ያለኝ። እርምጃው ግን ትክክል አይመስለኝም” በማለት የመንግሥትን እርምጃ አጣጥሏል።

በሌሎች አገሮች አሰራር መሰረት አከራካሪና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆነው የደህንነት ስጋት ያለባቸው ሰዎች ጥበቃ ይደረግላቸዋል በማለት “ለጃዋር ብለው ሌሎችን አደጋ ላይ መጣል የለባቸውም” በማለት በግሉ ጠባቂዎች መጠበቅ እንደሚችል ተነግሯል።

የጃዋር መሐመድ ጠባቂዎች ለደህንነታችን እንሰጋለን በማለት ከፌደራል ፖሊስ አባልነታቸው እና አስተማማኝ ዋስትና ከነበራቸው ሥራ ይልቅ የአንድ ግለሰብ ጠባቂ ሆነው መቅረታቸው ብዙ እያነጋገረ ይገኛል::

LEAVE A REPLY