በአፍሪካ ጉዳይ የውጭ ኃይሎች ጣልቃነት ገብነት አሳሳቢ መሆኑን ምሁራን ገለጹ

በአፍሪካ ጉዳይ የውጭ ኃይሎች ጣልቃነት ገብነት አሳሳቢ መሆኑን ምሁራን ገለጹ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ በአፍሪካ እየተስፋፋ የመጣውን የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በጋራ መዋጋት እንደሚገባ በ33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የታደሙ ምሁራን እና ባለሙያዎች ገለጹ።

የአፍሪካ ህብረት ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ ከጦር መሳሪያ ድምጽ ነፃ የሆነች አፍሪካን የመፍጠር ራዕዩን ከዓመታት በፊት ይፋ አድርጎ ነበር። በፈረንጆቹ 2005 በአፍሪካ ግጭት የተከሰተባቸው አገራት ብዛት ስድስት ሲሆኑ፣ በጦር መሳሪያ የታገዘ ግጭት የነበረባቸው ደግሞ ሰባት አገራት ነበሩ ተብሏል።

አሁን ላይ ግጭት ያለባቸው አገራት ቁጥር ከስድስት ወደ 17 ሲያድግ በጦር መሳሪያ የታገዘ ግጭት ያለባቸው የአፍሪካ አገራት ቁጥር ደግሞ ከ7 ወደ 21 ከፍ ብሏል። ይህም ህብረቱ ከጦር መሳሪያ ድምፅ ነፃ የሆነች አፍሪካን ለማየት ያሰበው እቅድ የመሳካት እሉንል እጅጉን ጠባብ አድርጎታል ነው ያሉት ምሁራኖቹ።

የመንግሥታት እና የፖለቲከኞች ሽኩቻ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት እያበዛና የሚፈጸመው የአሸባሪዎች ጥቃትም እየከፋ መምጣቱና ከሊቢያ እስከ ምስራቅ አፍሪካ ከባድ ቀውስ እያስከተለ ያለውን የሽብር አደጋ በጋራ መከላከል ይገባልም ብለዋል።

ተሳታፊ ምሁራኑ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ውስጣዊ ችግር ቀዳሚው የአፍሪካ የደህንነት የስጋት ምንጭ መሆኑን ጠቁመው፤ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች እና አካታች ያልሆኑ የልማት እንቅስቃሴዎች የሚፈጥሯችው ቅራኔዎችም ለዚህ ምንጭ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የውጭ ኃይሎች የግል ፍላጎትን ለማሳካት የሚያደርጉት ፍትጊያ እና የእጅ አዙር ጦርነት፣ እንዲሁም የአሸባሪዎች እና ጽንፈኞች እንቅስቃሴ አህጉሪቷን ዋጋ እያስከፈላት ነው ካሉ በኋላ፤ ምሁራኑ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ በማጠናከር የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት መከላከል እንደሚገባም አስታውቀዋል። አሁን ላይ በአፍሪካ በልማት አጋርነት ስም እየገቡ ያሉ የውጭ ሃይሎች ከልማት አጋርነታቸው ይልቅ ሴራቸው የበዛ በመሆኑ አንድነትን ማጠናከር መፍትሄ መሆኑንም አስረድተዋል።

LEAVE A REPLY