በግንቦት 12 ከተሞች ከታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተባለ

በግንቦት 12 ከተሞች ከታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ላይ 12 ከተሞች ከታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቀ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ሽፋን እና ተደራሽነቱ 44 ከመቶ ብቻ ነው። ከዚህ ውስጥም 33 በመቶ የሚሆኑት፣ ከዋናው የኤሌክትሪክ ቋት አገልግሎቱን የሚያገኙ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 11 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከታዳሽ ኃይል አገልግሎትን እየተጠቀሙ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት እና በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የኤሌክትሪፊኬሽን መርሀ ግብር ነድፎ እየሠራ ነው። እየተከናወነ በሚገኘው በዚህ መርሀ ግብርም የመብራት አገልግሎት ያልደረሰባቸው 12 ከተሞች ተመርጠው ከታዳሽ ኃይል አገልግሎቱን እንዲያገኙ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየተሠራ እንደሚገኝ ተቋሙ ይፋ አድርጓል።

በሁሉም ክልሎች የሚገኙት እነዚህ 12 የወረዳ ከተሞችም አሁን ላይ ሥራቸው እየተገባደደ መሆኑን ነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ የተናገሩት። በግንቦት ወር የኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት ከሚያገኙት ከተሞች መካከልም በኦሮሚያ ክልል 3፣ በአማራ ክልል 2፣ በትግራይ ክልል 1 እንዲሁም በደቡብ ክልል ደግሞ 2 ከተሞች ይገኙበታል።

በተጨማሪ በሌሎቹ ክልሎችም አንዳንድ ወረዳዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል። ከተሞቹ እስካሁን የመብራት አግልገሎት ተጠቃሚ መሆን ያልችሉ ናቸው ያሉት አቶ ሽፈራው፤ በግንቦት ወር ላይ የኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት ሲያገኙም፣ 70 ሺህ ሰዎች ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።

ከተሞቹ ከታዳሽ ኃይል ወይም ከፀሀይ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤሌከትሪክ አገልግሎት፣ በአሁኑ ሰዐት በፀሀይ ኃይል የሚሠሩ ፓናሎችን እየተተከ ይገኛል። የከተማ የውስጥ ለውስጥ የመስመር ኔትዎርክ ዝርጋታም በአገር ውስጥ የሥራ ተቋራጮች እየተሠሩ መሆናቸውን ነው ዋና ስራ አስፈፃሚው የገለፁት።

12ቱ ከተሞች ከታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተያዘላቸው እቅድ መሰረት እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ለኃይል ማመንጫ ሥራው ብቻ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ መደረጉን ጠቁመው ፤ በቀጣይም 25 ከተሞች ወደ ግንባታ እንደሚገቡና የዲዛይን እና የጨረታ ሥራዎች ተሠርተው ለአፍሪካ ልማት ባንክ ተልኳል ብለዋል።

LEAVE A REPLY