ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ድንበር ላይ ምዝገባ ተከለከሉ

ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ድንበር ላይ ምዝገባ ተከለከሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አሁን ላይ በድንበር አካባቢ የተሰማውና ተግባራዊ እየሆነ ያለው የኤርትራ ስደተኞችን ያለመመዝገብ ሂደት ስደተኞችን እያስጨነቀ ይገኛል።

ኤርትራውያን ከአገራቸው ወጥተው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በድንበር አካባቢ ምዝገባ እንደሚደረግ ይታወቃል። ከዚያ በኋላም ወደ ምዕራብ ትግራይ እንዳ’ባጉና ከተማ ይጓዙነበር። በዚህ ቦታም ስለግለሰቦቹ አስፈላጊው መረጃ ከተጠናቀረ በኋላ ወደ ስደተኞች መጠለያ እንዲገቡ የሚደረግበት አካሄድ ነበር።

ዛላንበሳ ድንበር ፋፂ ከተማ እስካሁን ኤርትራውያን ስደተኞችን እየመዘገቡ ሲያስገቡ የነበሩ የፌደራል መንግሥት የስደተኞችና የስደት ተመላሾች ተቋም ሠራተኞች ‘አንመዘግብም’ ማለታቸውን ቢቢሲ ስደተኞቹን አነጋግሮ ዘግቧል። ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገችና በኤርትራ ወታደር የነበረች ስደተኛ ከጓደኛዋ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጣ ከገባች ስድስት ቀን እንደሆናት ተናግራለች።

ሆኖም ፋፂ አካባቢ የሚገኙ ስደተኞችን የሚመዘግቡ አካላት ሊመዘግቧቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ጠቁማ “ወታደሮች እንደነበርንና ለድንበር አሻጋሪ ደላሎች 40 ሺህ ናቅፋ ከፍለን እንደመጣን ነገርናቸው። የመጣችሁበትን ቦታ  በግልጽ ተናገሩ አሉን። ምን ያህል ቀን እንደተጓዝን እና ሠንዓፈ ከተማ እንደደረስን አስረዳን።  ቦታውን በግልጽ አላወቃችሁትም። ሁለታችሁ የምትናገሩት ሰዐት የተለያየ ነው። ስለዚህ አንመዘግብም’ አሉን” ብላለች።

ጓደኛዋም፣ ወታደር እንደነበረች፣ የነበረችበትን የሚያስረዳ መታወቂያ ብታሳይም ሊመዘግቧት ፈቃደኞች ሳይሆኑ መቅረታቸውን አስታውቃለች። ቢቢሲ አደረግኹት ባለው ማጣራት ፋፂ ላይ ወታደር የነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ተመዝግበው መግባት እንዳልቻሉ እና መቆያ አጥተው መቸገራቸውን መረዳት ችሏል። እነዚህ ወታደር የነበሩ ስደተኞች በአሁኑ ሰዐት በፋፂ በግለሰቦች ቤት ለመቆየት የተገደዱ ሲሆን፣ ወደ ኤርትራ መመለስ ስለማይችሉም እግራቸው ወደመራቸው የትግራይ ከተሞች ለመሄድ መገደዳቸውን ይናገራሉ።

በይፋ አይነገር እንጂ የፌደራል መንግሥት ከኤርትራ የሚመጡ ስደተኞች አቀባበል ላይ አዲስ መመዘኛ መስፈርት ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል የሚሉ መረጃዎች አፈትልከው በመውጣት ላይ ናቸው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እነዚህ በፋፂ የሚገኙ የፌደራል መንግሥቱ ሠራተኞች ግን ይህንን መረጃ ሊያረጋግጡ አልፈለጉም። ይሁን እንጂ ወታደሮችና የመንግሥት ሠራተኞች ከነበሩ ስደተኞች ውጪ ሌሎች እንዳይመዘገቡ ትዕዛዝ መሰጠቱን ከምንጮቹ መረዳት ችሏል። ይህ አሰራር በቃል የተላለፈ እንጂ በጽሑፍ የተሰጠ ነገር አለመሆኑንም እነዚህ ምንጮች አክለው አስረድተዋል።

በአሁኑ ጊዜ የስደተኛ መጠለያዎች ባይዘጉም አሁን ባለው ሁኔታ ግን እንደማይቀጥሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ በፊት ድንበር አቋርጠው ቤተሰቦቻቸው ወደሚገኙባቸው የተለያዩ የትግራይ ከተሞች ያቀኑ ስደተኞች ወደ ስደተኞች መጠለያ ሄደው ለመመዝገብ ሲጠይቁ ወደ ድንበር ተመልሰው ይመዘገቡ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን መዝጋቢዎቹ ‘የት ቆይታችሁ ነበር? እና በየት በኩል አለፋችሁ?’ በሚል ጥያቄ እንደማይመዘግቧቸው ስደተኞቹ አመላክተዋል።

በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ እማኞችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ። ከነዚህም መካከል የፋፂ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ደጀኔ ሐጎስ ናቸው። ” ብዙ ኤርትራውያን ልጆች ይዘው፣ ለደላሎች ገንዘብ ከፍለው፣ ከድንበር ጠባቂዎች ተደብቀው፣ እዚህ ከደረሱ በኋላ አንመዘግባችሁም በመባላቸው ሲቸገሩ አይቻለሁ። ለምሳሌ በቅርቡ ከ40 በላይ ስደተኞች አዝነው እያለቀሱ ወደ ኤርትራ ሲመለሱ ተመልክቻለሁ” ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል::

LEAVE A REPLY