ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሱዳን የቀድሞውን ፕሬዝደንት ኦማር አል-በሽርን ለዓለም ዐቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አሳልፋ ልትሰጥ እንደሆነ ተነገረ። ሱዳን አል-በሽርን አሳልፋ የምትሰጠው በቀረበባቸው የጦር ወንጀል ክሶች ነው ተብሏል።
የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝደንት እ.አ.አ 2003 ላይ በዳርፉር ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ በዘር ማጥፋት፣ በጦር ወንጆሎችና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ክሶች ቀርቦባቸዋል። በሄግ የሚገኘው ዓለም ዐቀፉ የጦር ወንጀሎች ፍርድ ቤት ዐቃቢ ሕጎች የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝደንት የቀረበባቸውን ክሶች በሄግ ተገኝተው እንዲከላከሉ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዳርፉር በነበረው ጦርነት በትንሹ የሞቱት ሰዎች 300,000 እንደሚደርሱ እና ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎችም መፈናቀላቸውን ገልጿል። ከሁለት ወራት በፊት አል-በሽር በቀረቡባቸው የሙስና ወንጀል የሁለት ዓመት እስር ተበይኖባቸው ነበር።
የአል-በሽር አገዛዝ በወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ተጀምሮ፤ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ፍፃሜውን አግኝቷል። ባሳለፍነው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ከሥልጣን የተወገዱት አል-በሽር፤ በመፈንቅለ መንግሥት እ.አ.አ 1989 ላይ ነበር ወደ ሥልጣን የወጡት።
አል-በሽር ሥልጣን ሲቆናጠጡ በደቡባዊ እና ሰሜናዊ ሱዳናውያን መካከል በተከሰተ የእርስ በርስ ጦርነት አገሪቱ ስትታመስ የነበረበት ወቅት ነበር። ሱዳን በአል-በሽር አገዛዝ መባቻ ግድም የተረጋጋች ብትመስልም ግጭቱ እንደ አዲስ ሲያገረሽ፤ አል-በሽርም ዳርፉር አካባቢ ከባድ የጦር ኃይል ተጠቅመዋል በሚል ተወቅሰዋል።
ጫና የበረታባቸው አል-በሽር ግን በአውሮፓውያኑ 2010 እና 2015 የተደረጉ ምርጫዎችን በማሸነፍ መንበራቸው ላይ ተደላድለው ተቀምጠዋል። በአይሲሲ የእስር ማዘዣ የወጣባቸው አል-በሽር ከአገራቸው ውጭ በተገኙበት እንዲያዙ ቢወሰንባቸውም ወደ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ አራቢያ እና ደቡብ አፍሪቃ ከመሄድ ግን ያገዳቸው አልተገኘም ነበር።
2015 ሰኔ ወር ላይ (እ.ኤ.አ) ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሆነው ሊያዙ መሆናቸውን የሰሙት አል-ባሽር ሹልክ ብለው የወጡበት መንገድ በጊዜው የዓለም ቀዳሚ መወያያ ጉዳይ ለመሆን ችሎ ነበር።