ይች አገር በእውነት ላይ የተመሰረት፣ ፍትህን ማዕከል ያደረገ እርቅ ትፈልጋለች። የማስመሰል ወይም ለፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን እውነተኛ እርቅ። ተበዳይ የበደሉ ልክ ታውቆ ይቅርታ የሚጠየቅበት እና የሚካስበት፣ በዳይ የወንጀሉ ልክ በበቂ ማስረጃ ተረጋግጦ እንደየ ክፋቱ መጠን በይቅርታ ወይም በቅጣት የሚታረምበት፣ የቂም ምዕራፍ የሚዘጋበት፣ የአግላይና ተገላይ ፖለቲካ የሚያበቃበት፣ የተሰበረ የሚጠገንበት፣ የሰባሪነት መንፈስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከፖለቲካችን የሚጠፋበት፣ በመናናቅ ፋንታ መከባበር የሚነግስበት እውነተኛ እርቅ ይች አገር ትፈልጋለች።
በደረሰባቸው እና ዛሬም እየደረሰባቸው ባለው በደል እና ግፍ ያቄሙ አሉ፣
ከአንዱ ሰባሪ ወደ ሌላ ሰባሪ ተሸጋገርን ብለው በፍርሃት እና ስጋት ቆፈን የተሸበቡ ዛሬም አሉ፣
+ በሕዝብ ላይ በፈጸሙት በደል ጸጸት ሳይሰማቸው በደነደነ ልባቸው ዛሬም ለሌላ ዙር ግጭት እና መጠፋፋት ያቆበቆቡ አሉ፣
+ በይቅርታ የማይሰረይ ወንጀል ሰርተው በአደባባይ የሚንጎማለሉም አሉ፣
+ ተገፍተውም፣ ተበድለውም ልባቸውን ለይቅርታ በርገግ አርገው ከፍተው ተበዳዮች የሚጸጸቱበትን ቀን እንደ ምጽአት የሚጠባበቁም አሉ፣
+ ትላንት የሰበራቸውን ሊሰብሩ፣ ያዋረዳቸውን ሊያዋርዱ፣ ያሳደዳቸውን ሊያሳድዱ፣ ያፈናቀላቸውን ሊያፈናቅሉ ዛሬም በበቀል ስሜት የሚንተገተጉ እና ለርምጃም ያቆበቆቡም አሉ፣
እንዲህ ውጥንቅጡ በወጣበት የአገራችን ፖለቲካ እርቅን፣ ሰላምን፣ ፍትሕን፣ መቻቻልን ያመጣሉ የተባሉት ጠቅላያችን በሰባሪና ተሰባሪ አዙሪት ተጠልፈው መውደቃቸው ቀጣዩን ጉዟችንን እጅግ እጅግ ያከብደዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ወደ ባሌ ወርደው ለህዝብ በአደባባይ ያደረጉትን ንግግር ዶ/ር አብረሃም አለሙ እንደተረጎመው ከሆነ በህዝብ ውስጥ የበለጠ ቁርሾን፣ ቂምን እና ጥላቻን የሚዘራ እና ጸብ አጫሪም ሆኖ ነው ያገኘሁት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚኛ ባደረጉት ንግግራቸው ላይ፤
‘ትናንት ንቆን፣ ሰብሮን፣ ዘርፎን፣ ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ሁሉ ግጦ የወሰደን፣ ልጆቻችሁ ታግለው፣ ሰባብረው፣ ከኦሮሚያ እንብርት አባረው ካስወጡት ጋር ከመቆም ሞት ይሻላል። ትናንትና ያዋረደንን፣ አዋርደነዋል፤ ትናንት የሰበረንን ሰብረነዋል። ትናንትና አትወጡም አትገቡም ብሎ አጥር ያጠረብን ዛሬ ወጥቶ መግባት አይችልም፣ ከእኛ ፈቃድ ውጪ።’
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከላይ በተተረጎመው መልኩ ተናግረው ከሆነ ይህ ንግግራቸው የገባንበትን ሌላ የቂም አዙሪት ነው የሚያሳየው። በሳቸው ደረጃ ያለ እና ይህን ለውጥ ከቂም እና ከጥላቻ በራቀ መልኩ ያሸጋግራል የተባለ ሰው እንዲህ ያለ ቂም ቆጠራ ውስጥ ከገባ መቆሚያው የቱ ጋር ነው የሚሆነው? መፈራረጅስ ከተጀመረ ለመሆኑ እሳቸውም ሆኑ በዙሪያቸው ያሉ የመንግስት ባለሥልጣናት ትላንት በተፈጸመው ነገር ከሰባሪው ነው ወይስ ከተሰባሪው የሚፈረጁት?
የመጀመሪያ የፓርላማ ንግግራቸው ላይ ለሃያ ሰባት አመት ሰባብረን፣ አሸብረን አሰቃይተናችኋል እና ይቅርታ አድርጉልን ያሉት ተዘነጋ እንዴ? እርግጥ ነው ይች ምርጫ ብዙ ታስለፈልፋለች። ፖለቲከኞች ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ብዙ ይናገራሉ፤ በዛውም ልክ ብዙ ይስታሉ። በየንግግራቸው መሃል የአፍ ወለምታ አይጠፋም። አንዳንዱ የአፍ ወለምታ ግን በተለይም በጠቅላዩ ደረጃ ባለ ሰው አንደበት ሲነገር በአገር ፖለቲካ ላይ ጥቁር ጥላ እንዲያጠላ ያደርጋል።
ትላንት በተፈጸመው ጥፋት፣ ሰበራ፣ አፈና እና ዝርፊያ ህውሃትን ብቻ ተጠያቂ አድርጎ መሄድ ከየትስ ያደርሳል? የሰባሪና ተሰባሪንስ ጎራ መቀላቀሉ ለማን ይበጃል? የሚሻለው ያሳለፍናቸውን ችግሮች፣ መከራዎች፣ የሰባሪ እና ተሰባሪ ትርክት እንደ ጋራ ችግር፣ የጋራ ፈተና አድርጎ በመቁጠር ዘላቂ የሆነና የማያዳግም መፍትሔ በጋራ መፈለግ አይሻልም ወይ?
ወጣቱ እንኳን ቂም እና በቀል ተነግሮት እንዲሁም በቋፍ ነው። የመጣንበት እረዥምና ብልሹ የፖለቲካ መንገድ ሆደ ባሻ፣ በትንሹ የሚገነፍሉ፣ ጭካኔም ያደላቸው፣ ከማህበረሰቡ ወግና ልማድ ያፈነገጡ፣ በተናጠል እንደ ሰው ሳይሆን በደቦ የሚያስቡ እና በስሜት ያሰቡትን የሚፈጽሙ ወጣቶችን አፍርቷል። በሞራልም ሆነ በስነ ምግባር የተሰበረ ወጣት ፈጥረናል።
በዚህ ላይ ይባስ ብሎ ፖለቲከኞች እዳሰኛቸው የሚወረውሩት ቃላት በወጣቶቹ አዕምሮ ውስጥ የተዳፈነውን እሳት እንዲንቦገቦግ ነዳጅ እየሆነ ነው። ዛሬ ለበቀል ያነሳሳናቸው ወጣቶች ወገናቸውን ሲያጠቁ ደግሞ መልሰን እንወነጅላቸዋለን። የሞራል ከፍታችንን ልናሳይም በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እንልና እናወግዛቸዋለን።
ጠቅላዩም ሆኑ ሌሎች ፖለቲከኞች እንዲህ ካሉ ማህበረሰቡን ለቁርሾና ለሌላ የግጭት አዙሪት የሚገፉ ንግግሮች ከማድረግ ሊታቀቡና ከአዙሪቱ ሊርቁ ይገባል። እሳት ላይ የተጣደች አገር ይዞ የነዳጅ ያህል እሳት የሚያስነሱ ቃላቶችን እየረጩ ሰላም ሊመጣ አይችልም። ሰበራና ብልጽግናም አብሮ አይሄድም።
ይልቅ ህውሃትን ጨምሮ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ የእርቅ ጉባዔ ማድረግ ከገባንበት አጣብቂኝ ያወጣናል። ይች አገር በእውነት ላይ የተመሰረተ እና ፍትህ ተኮር እርቅ ሳይውል ሳያድር ትሻለች። ዛሬም ስለፍትህ እና ስለ እውነተኛ አገር አድን እርቅ እንጮሃለን።
ቸር እንሰንብት