ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የ5 ሴት ወጣቶች ህይወት እንዲጠፋ ያደረገው ግለሰብ በሞት እንዲቀጣ መወሰኑን የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለጸ ።
የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ ሐኪም ሲራጅ አብዱከሪም ጣሂር አብደላ የተባለው ግለሰብ ነዋሪነታቸው በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጉርሱም ወረዳ ዳይፈርስ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የሆኑ ወጣት ሴቶችን በህገ ወጥ መንገድ በማስኮብለል ለህልፈተ ህይወት በመዳረጉ ቅጣቱ ተላልፎበታል ብለዋል።
“በጎረቤት አገር በኩል ሳውድ አረቢያ ወስጄ በከፍተኛ ደመወዝ ስራ እንድትቀጠሩ አደርጋለሁ ” በሚል ማታለያ በ2010 ዓም በተለያዩ ቀናትና ወራት ከቀያቸው ካስኮበለላቸው 8 ወጣት ሴቶችን ላይ ከእያንዳንዳቸው 3 ሺህ ብር በመቀበል ዘመድ አዝማድ ሳይሰማ ከአደጉበት ቀዬ ጭለማን ተገን በማድረግ ካስኮበለላቸው 8 ሴቶች መካከል በጀልባ መስጠም ምክንያት 5ቱ ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል። በደላላ አማካኝነት ቤተሰቦቻቸውን በማስጨነቅ ከእያንዳንዳቸው ቤተሰብ 10 ሺህ ብር መቀበሉም ታውቋል።
ከአደጋው የተረፉት ወደ ቀያቸው እንደተመለሱ ለሟች ዘመዶች በሰጡት ጥቆማ መሰረት የክስ አቤቱታ የደረሰው የጉርሱም ወረዳ ፖሊስ ወንጀለኛውን አብዱከሪም ጣሂር አብደላ በቁጥጥር ስር በማዋል ክስ ተመስርቶበት የምርመራ መዝገቡ አጣርቶ ለማየት ስልጣን ላለው ለምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲተላለፍ አድርጎ ነበር።
ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ግለሰቡ ወንጀሉን መፈጸሙ በአቃቢ ህግ፣ በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማረጋገጥ የቅጣት ማቅለያና ማክበጃ ከመረመረ በኋላ፤ አላግባብ ጥቅም ለማግኘት ሲል አምራች ኃይል በሆኑት ወጣት ሴቶቹ ላይ የተፈጸመው ድርጊት አሰቃቂ ወንጀል በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጥር 2 ቀን 2012 በዋለው ችሎት ወንጀለኛው አብዱከሪም ጣሂር አብደላን በሞት እንዲቀጣ መወሰኑን ይፋ አድርገዋል። ይህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተፈፃሚ የሚሆነው ለአገሪቷ ፕሬዚዳንት ቀርቦ ይሁንታ ሲያገኝ ብቻ ነው::