የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃና የኤክሳይዝ ታክስ አዋጆች በፓርላማ ፀደቀ

የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃና የኤክሳይዝ ታክስ አዋጆች በፓርላማ ፀደቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጥላቻ ንግግርን እና ሀሰተኛ መረጃን ለመቆጣጠር የወጣውንና የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጆችን ዛሬ ባደረገው ልዩ ስብሰባው አጽድቋል።

የጥላቻ ንግግርን እና ሀሰተኛ መረጃን ለመቆጣጠር የረቀቀው ሕግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከወትሮው የተሻለ ይዞታ ላይ ይገኛል የሚባልለትን ሀሳብን የመግለጽ ነፃነትን አደጋ ላይ ይጥላል በሚል ስጋታቸውን የሚሰነዝሩ በርካታ ናቸው::

በሌላ በኩል ሕጉ ምን ያህል ሊተገበር ይችላል በሚለው ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው የሚገልፁም አልጠፉም። የመንግሥት አካላት ደጋግመው አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በአገሪቱ ውስጥ ሰርክ የሚነሱ የብሔርም ሆኑ የሃይማኖት መልክ ያላቸው ግጭቶች እና ግርግሮች በተለይ በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች በሚሰራጩ እና ጥላቻ በሚታጨቅባቸው መልዕክቶች የሚባባሱ ምናልባትም የሚያነሳሱ ናቸው በማለት ይከራከራሉ።

በኢፌድሪ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎች መካከል፣ ትልቁ የሕግ እና የፍትህ ማሻሻያ ነው የሚሉት የተቋሙ ቃል አቀባይ አቶ ዝናቡ ቱኑ፤ የሕጉን አረቃቅ ሂደት፤ “የሕግ እና የፍትሕ ማሻሻያ ሥራ ድሮ በተለመደው መንገድ እንዲሄድ ታሳቢ የተደረገ አይደለም ” ሲሉ ይገልጹታል::

ዋነኛ ሥራው ህግን ማርቀቅ ፣ እንዲሁም ማስረፅን ያደረገ ራሱን የቻለ መምርያ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽሕፈት ውስጥ ይገኛል። መምርያውን በተግባራቱ ሊያግዝ የሚችል እና ፍፁም ገለልተኛ ነው የሚሉት  አቶ ዝናቡ የሕግ እና የፍትሕ አማካሪ ምክር ቤት መኖሩንና ምክር ቤቱ በተለይ ትላልቅ የሚባሉ ሕግጋትን በማርቀቅ ረገድ የጠቅላይ አቃቤ ሕግን እንደሚያማክር አስታውቀዋል።

“ከመንግስት ባሻገር በዘርፉ ውስጥ ሰፊ ልምድ ያላቸው ዕውቀትም ያላቸው፣ ክህሎትም ያላቸው፣ ልምድ ዕውቀት እና ክህሎታቸውን ለሕዝባቸው አገልግሎት መስጠት የሚፈልጉ ሰዎች ያሉበት ነው” ያሉት ሓላፊ፤ አማካሪ ምክር ቤቱ ሦስት ዋና ዋና ሥራዎችን እንዲሰራ መፈለጉን ይጠቁማሉ::

የዚህ ምክር ቤት ቀዳሚ ዓላማ ጨቋኝ ናቸው የሚባሉና የሚያፍኑ ነበሩ ያሏቸውን ሕግጋት ማሻሻል ነው። ሁለተኛው አሁን የተደረሰበትን ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ አዳዲስ ሕግጋትን ማርቀቅን፤ ሦስተኛው ደግሞ እነዚህ ሕግጋትን ነፃ እና ገለልተኛ ሆኖ በመገምገም ባለድርሻ አካላትን በማወያየት ለመንግሥት እንዲቀርብ ማድረግ ነው ተብሏል።

“ሆኖም ይህ ምክር ቤት የሚያግዘን አንድ ቡድን ነው። በዋናነት ግን የጥላቻ እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተዘጋጀው ይህ ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀው በተቋማችን አቅም፣ የሌሎችንም ባለድርሻ አካላትን ድጋፍ ወስዶ ነው” ሲሉ አቶ ዝናቡ ቱኑ ተናግረዋል።

የጥላቻ ንግግርን እና ጉዳት አድራሽ የሐሰተኛ መረጃዎችን ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው ሕግ መረቀቁ ከተሰማበት እና ረቂቅ ሕጉ ለውይይት ከቀረበበት ጊዜ አንስቶ ነው ስጋት እንደገባቸው የሚናገሩ አካላት ድምፅ መሰማት የጀመረው። የሰብዓዊ መብት ተከራካሪው ቡድን ሂውማን ራይትስ ዎች በወርሃ ታህሳስ ባወጣው ሪፖርት ሕጉ ከፍተኛ ማሻሻያ የማይደረግበት ከሆነ የመናገር ነፃነትን የመደፍጠጥ አቅም እንዳለው ፍራቻውን አሳውቋል።

በወቅቱ በሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ላይቲቲያ ባደር “የኢትዮጵያ መንግስት አንዳንድ ጊዜ በበይነ መረብ የሚሰራጩ ንግግርች እና አስተያየቶች ላባባሷቸው ማኅበረሰባዊ ግጭቶች ምላሽ አንዲሰጥ የሚደርስበት ጫና እየጨመረ ነው”  ብለው እንደነበር ይታወሳል::

ግጭትን መቀስቀስን እና ማነሳሳት ቀደም ሲል በፀደቁ የኢትዮጵያ ሕግጋትም የተከለከለ መሆኑን በማስታወስ የጥላቻ ሕግን እና ጉዳት አድራሽ ሐሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨትን ብቻ የሚመለከት ሕግ ማርቀቅ የተለየ ኃሳብን ያላቸው ሰዎች ላይ የፍርሃትን ቆፈን በመፍጠር ፀጥ የማሰኘት ዓላማ ሊኖረው ይችላል ሲል የሚሟገተው ደግሞ ጋዜጠኛ እና ጦማሪው በፍቃዱ ዘ ኃይሉ ነው።

“መንግሥት ራሱ እኮ ከጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃን ከማሰራጨት የነፃ አይደለም” ያለው በፍቃዱ ፤”የክልል መንግሥታት የሚያስተዳደሯቸውን የብዙሃን መገናኛዎች ተመልከቱ። በፕሮፓጋንዳ ጦርነት ተጠምደዋል። ይህ ጦርነትም አንዳንዴ በጥላቻ ይዘት ባላቸው ንግግሮች እና በሐሰተኛ መረጃዎች የተደገፈ ነው።” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል::

ለበፍቃዱ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተቀሰቀሱ የብሔር እና የኃይማኖት ግጭቶች የበይነ መረብ ስርጭት ተደራሽነት ዝቅ ባለባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ጭምር የተከሰቱ መሆናቸው መንግሥት አንደሚለው የማኅበራዊ ብዙሃን መገናኛዎች ሚና ከፍ ያለ እንዳልነበር ጠቁሞ ፤ ሕጉ ቢወጣም እንኳ በማኅበራዊ የብዙሃን መገናኘዎች የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግር እና ጉዳት አድራሽ ሐሰተኛ መረጃዎችን መቆጣጠርም የሚታሰበውን ያህል ቀላል እንደማይሆኑ ተናግሯል።

LEAVE A REPLY