ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢኮኖሚና የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ በየሴክተሩ ያሉ የአሠራር ክፍተቶች እየተለዩ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
በዛሬው እለት በኦሮሚያ ክልል በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ ችግሮቸን ለመቅረፍ በማለት በአዲስ አበባ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ ነው አቶ ሽመልስ አብዲሳ ይህንን ያሉት።
በመድረኩ ላይ በኦሮሚያ ክልል ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች እና የአሠራር ክፍተቶች ዙሪያ ከባለሀብቶች ጋር ምክክር መደረጉን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ያሳያል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ ቸግሮችን ለመቅረፍ መቀመጫውን ብሪታኒያ ካደረገው ቢግ ዊን ፋውንዴሽን ጋር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ የተጓተቱ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ማስገባት እና አዳዲስ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ እየሰጡ መሄድ ወሳኝ እንደሆነም ገልጸዋል።
እስካሁን በ66 ሴክተሮች ውስጥ ያሉ ችግሮችን የመለየት ሥራ ተሰርቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ሥራው ቀጣይነት ያለው መሆኑን እና ተመሳሳይ ችግሮችን ለመቅረፍ እና ዘርፉን ለማበረታታት የግሉ ሴክተር ሚና ወሳኝነት እንዳለው አስተረድተዋል።
በኦሮሚያ ክልል በሚከሰቱ ግጭቶች ሳብያ በርካታ ፋብሪካዎች እና የኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ በሚደርስ የቃጠሎ ጥቃት መውደማቸው ባለሃብቶች ወደ ክልሉ ገብተው እንዳይንቀሳቀሱ ማድረጉ ይታወቃል።
የኢንቨስተሮች ትኩረት ለማግኘት በክልሉ የሚኖሩ ማናቸውም ዜጎች ያለፍርሃት እንዲኖሩ ማስቻል እና የመንጋ እንቅስቃሴን በሕግ የበላይነት መቆጣጠር የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ተቀዳሚ ስራ ሊሆን እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎች ለኢትዮጵያ ነገ ገልጸዋል።