ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በህወሓት የምትተዳደረው ትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ፣ በ4 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
የካቲት 11 የሚከበረው 45ኛ ዓመት የህወሓት ምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ በመቐለ ከተማ በ4 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች በዛሬው ዕለት የምረቃ ሥነ ሥርዓታቸው ተከናውኗል፡፡
ለፖለቲካ ፕሮፐጋንዳ ታስቦ በተዘጋጀው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሩፋኤል ሺፋረ እና ሌሎች የክልሉ እና የከተማዋ ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች መገኘታቸው ታውቋል፡፡
መሰረተ ልማቶቹ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የአስፓልት መንገዶች እና የአግዓዚ አደባባይ መሆናቸው ተሰምቷል። ከምረቃ መርሃ ግብሩ በኋላ አመራሮች በአግዓዚ አደባባይ የችግኝ ተከላ ሥነ-ሥርዓት አከናውነዋል።
በሌላ በከተማዋ በ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ ለሚገነቡ ሆስፒታሎች፣ ዘመናዊ መናኸሪያ፣ ትምህርት ቤቶች እና ለሌሎች መሰረተ ልማቶች ትናንት የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡