ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ተጽእኖ ፈጣሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ እና ኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አባላቶቻችን እና ደጋፊዎቻችን በጅምላ እየታሰሩ ነው ሲሉ አቤቱታቸውን አሰሙ።
የኦነግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሚካኤል ቦረን ትናንት ረፋድ ላይ ፓርቲያቸው በሰጠው መግለጫ ላይ “ከ350 በላይ የሚሆኑ አባላቶቻችን እና ደጋፊዎቻችን ለእስር ተዳርገውብናል፤ ከሰሞኑ ደግሞ በበርካታ የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ እኛ በማናውቅም ምክንያት አባላቶቻችን እና ደጋፊዎቻችን በጅምላ እየታሰሩ ይገኛሉ።” ብለዋል:: የጅምላ እስር እየተጠናከረ እየሄደ ያለው ደግሞ የአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች እንደሆነም ጠቁመዋል።
በአንድ ሳምንት ብቻ በ7 የኦሮሚያ ዞኖች የሚገኙ 350 አባሎቻችን እና ደጋፊዎቻችን በጅምላ የታሰሩ ሲሆን፤ ይህን የጅምላ እስር እያደረገ ያለው ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ መሆኑን አውቀናል በማለትም መንግሥትን ወቅሰዋል።
በሌላ በኩል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ- ኦፌኮም ደጋፊዎቼ እና አባላቶቼ ለእስር እየተዳረጉብን ነው ብሏል። የፖርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የጽ/ቤት ሓላፊ የሆኑት አቶ ጥሩነህ ገምታ በቅርቡ 27 አባላት እና ደጋፊዎቻቸው ለእስር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
“በጥቅሉ 27 ሰዎች ታስረዋል። 23 አባላት እና 4 ደጋፊዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች የት ናቸው ቢባል፤ ጉጂ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ ጊምቢ ከተማ፣ የኦፌኮ ወጣት ሊግ ፊቼ ከተማ ላይ ዱጎምሳ የሚባል አባላችን ታስሯል። ሰበታ ላይ ብቻ 11 ሰዎች ታስረውብናል። ይህ እስር የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ መምጣቱን ያሳያል” ሲሉም ተደምጠዋል::
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ግን በፖለቲካ ተሳትፏቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ስለመኖራቸው የማውቀው ነገር የለም” ካሉ በኋላ “በክልላችን የፖለቲካ ፓርቲ አባል ስለሆነ ብቻ ማንም ሰው አይታሰረም መታሰርም የለበትም። በሌላ የወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው የታሰሩ ካሉ እሱን በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው አካል ማጣራት ያስፈልጋል” ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።
ለእስር የታደረጉት ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ የፖለቲካ ተሳትፎ ላይኖራቸውም ይችላል ሲሉ ሃሳባቸውን በማጠናከር፤ “የታሰሩበት ምክንያት በፖለቲካ ተሳትፏቸው ይሁን በሌላ ማወቅ በማይቻልበት ላይ እኔም ይህ ነው ማለት አልችልም።” በማለት ተከራክረዋል።
ከሁለት ቀናት በፊት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፤ ለአገሪቱ ደህንነት ሲባል ከዚህ በኋላ ማናቸውንም በወንጀል ድርጊት የሚሳተፉ አካላት አልታገስም ማለቱ አይዘነጋም።
ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ወንጀል ተፈጽሞባቸው በነበሩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን ቁጥጥር ሥር እያዋለ እና ክስ እየመሰረተ መሆኑንም አስታውቋል::