ብዙ ሰዎች እንደዋዛ ተመልክተውታል፤ ነገር ግን ብዙዎቹን የፖለቲካ ድርጅቶች ከጫወታ ውጪ ሊያደርግ የሚችል ነገር ነው። የተቀመጠለት የሁለት ወር የጊዜ ገደብ አንድ ወሩ አልቋል፤ ነገር ግን በተጠየቀው መሠረት የዳግም ምዝገባ ማመልከቻውን አስገብተው እየታየላቸው ያሉት ሕወሓት እና አረና ብቻ ናቸው።
ብዙዎቹ ፓርቲዎች አዋጁ ሲፀድቅ ጀምሮ ተቃውሞ ላይ ነው የከረሙት። መሥፈርቱን በጊዜ ገደቡ ያላሟሉ ድርጅቶች ከምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ ይሰረዛሉ። የተሰረዙት ወይም ሌሎች ለምርጫው ለመወዳደር ከዕጩዎች ምዝገባ ቀን በፊት (በተለዋጭ ፕሮግራሙ መሠረት ከሚያዝያ 13 እስከ ሚያዝያ 26) ድረስ አዲስ ፓርቲ የሚመዘገብበትን ሒደት በሙሉ አሟልተው በመምጣት ተመዝግበው ነው ለምርጫ ሊደርሱ የሚችሉት። ይህ ደግሞ ጥቂት መሥፈርት ማሟላት ለከበዳቸው ፓርቲዎች እንደ አዲስ ይመዘገባሉ ብሎ መጠበቅ የማይመስል ነገር መጠበቅ ነው። የትኞቹ ፓርቲዎች ይሳካላቸው ይሆን? የትኞቹስ ከምኅዳሩ ይሰናበቱ ይሆን?
ሕጉ ምን ይላል?
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ “የመሸጋገሪያ ድንጋጌ” (እንቀፅ 160) እንደሚለው “ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት የተመዘገባ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በዚህ አዋጅ የተቀመጡትን መሥፈርቶች ቦርዱ በሚያስቀምጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲያሟላ ያደርጋል”። በዚሁ መሠረት ምርጫ ቦርድ ታኅሣሥ 26፣ 2012 ባፀደቀው “ተመዝግበው የሚገኙ የአገር ዐቀፍና የክልል ፓርቲዎች ማሟላት ያሉባቸው” መሥፈርቶች መመሪያ ላይ “ሁሉም ተመዝግበው የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዋጅ 1162/2011 የተቀመጠውን የመሥራች አባላት ፊርማ ለማሟሟላት የሁለት ወራት የጊዜ ገደብ አላቸው” የጊዜ ገደቡ የፊታችን የካቲት 26 ይጠናቀቃል። ብዙዎቹ ፓርቲዎችም ከጅምሩ የተቃወሙት ይህንን ነበር።
ፓርቲዎቹ የማስፈረም ሒደት
በአዋጁ እና በመመሪያው መሠረት አገር ዐቀፍ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸው ቢያንስ የ10ሺሕ መሥራች አባላት ፊርማ ነው። በተጨማሪም ከነዚህ ፈራሚዎች መካከል ከአንድ ክልል የሚመጡት ከ40 በመቶ በላይ እንዲሆን አይፈቀድም። ዋና ዋናዎቹ የብሔር ፓርቲዎች (አብን እና ኦፌኮን ጨምሮ) የተመዘቡት አገር ዐቀፍ ፓርቲ ተብለው ነው። ስለሆነም እያንዳንዳቸው መሠረቴ ከሚሉት ክልል ውጪ ቢያንስ 6 ሺሕ የመሥራች አባላት ፊርማዎች መሰብሰብ ይጠበቅባቸዋል። ይሁንና የሁለቱን ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ጠይቄ የተሰጠኝ መልስ “የሚጠበቁብንን ፊርማዎች ሰብስበን ወደ ምርጫ ቦርድ ለመሔድ ዝግጅት ላይ ነን” የሚል ነው።
ኢዜማ በበኩሉ ቀድሞ ካስገባሁት ፊርማ በተጨማሪ የተወሰኑ ፊርማዎችን አሰባስቤ ወደ ምርጫ ቦርድ ለመሔድ እየተዘጋጀሁ ነው ብሏል። የኢትዮጵያ አገር ዐቀፍ ንቅናቄ ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት ጋር ስደውልም የተሰጠኝ መልስ ተመሳሳይ ነው። “እኛ በተለያየ ሁኔታ ፖለቲካው ውስጥ እውቅና ስላለን እንዲሁም የፖለቲካ ሁኔታው ያሳሰባቸው ብዙ ሰዎች ስላሉ ፊርማ መሰብሰቡ ላይ ያን ያህል አልተቸገርንም” አሉኝ። ነገር ግን “አሠራሩ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፤ 1500 ፊርማ በቂ ነው ተብሎ ከ2 ወር በፊት ነበር ሰርተፊኬት የተሰጠን። በሁለት ወር ውስጥ 8500 ፊርማ ጨምሩ ማለት ፍትሐዊ አይደለም። ግን እየተሠራ ያለው በዘመቻ ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም” በሚል ነው የተጠየቅነው ተጨማሪ ፊርማ ማሰሰባሰብ የጀመርነው በሚል በሒደቱ ያላቸውን ቅሬታ ነግረውኛል። ሌሎች በርካታ ፓርቲዎች ግን ይህን ማሟላት ስለሚቸግራቸው ወደ ውህደት እየተሯሯጡ መሆኑን ሰምቻለሁ።
በሌላ በኩል ክልላዊ ፓርቲዎች 4 ሺሕ ፊርማ ይጠበቅባቸዋል። ከ10 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ሕዝብ ቁጥር ያላቸው ብሔሮችን መሠረት አድርገው የሚመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ የፊርማ ቁጥር ገደቡ እንደማይመለከታቸው በመመሪያው ላይ ተገልጿል።
የዛሬ ወር ምን እንጠብቅ?
በቀሪዎቹ 20 ቀናት ውስጥ እየጨረስን ነው ያሉት ፓርቲዎች የዳግም ምዝገባ ማመልከቻዎቻቸውን ያስገባሉ። ነገር ግን የምዝገባ ሰርተፊኬት ካላቸው ከ70 በላይ ከሆኑት ፓርቲዎች ውስጥ ከሃምሳ በላይ የሚሆኑት አለጥርጥር ከመድረኩ ይሰናበታሉ። ጥያቄው እርምጃው ፍትሓዊ ነው ወይ የሚለው ይሆናል።
የመደራጀት መብት በተቻለ መጠን የሚከበረው የመደራጀት ቅድመ ሁኔታዎች ቀላል ሲሆኑ ነው። ነገር ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደሚታየው ዓይነት የግለሰቦች ፓርቲዎች የሚታዩበት መሆኑ ብዙኀኑን ከማደናገር የበለጠ ፋይዳ ሊኖረው ይችላል። የተለያዩ ሕዝባዊ ዕውቅና ያላቸውን የፖለቲካ ድርጅቶችን እየደወልኩ በጠየቅኩበት ወቅት የተረዳሁት በሒደቱ ቅሬታ ቢኖርባቸውም ይህ መሥፈርት ከዳግም ምዝገባ እንደማያግዳቸው ነው። ስለሆነም ከዳግም ምዝገባው በኋላ የሚቀሩት ፓርቲዎች ጥቂት ቢሆኑም የየራሳቸው መሠረት ያላቸው እና ለምርጫው ከፍተኛ ተፎካካሪ ሆነው የሚቀርቡ መሆናቸውን ከወዲሁ መጠበቅ ይቻላል።
ምንጭ ፡ – DW