ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ስመ ገናናውና ተወዳጁ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ቅዳሜ የካቲት 14 ቀን 2012 ዓ.ም ታላቅ የሙዚቃ ድግስን ለማቅረብ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ከአስተባባሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
ብዙዎች በተለያዩ የማኅበራዊ ድረገፆች “ንጉሡ የሚራቀቅበት መድረክ በጥንቃቄ ተዘጋጅቷል፣ ከተማይቱ የሚገኙ አድናቂዎች በዓል እስኪመስል ድረስ ደምቃ ትውላለች፣ ታመሻለች። ታላቁ ጥበበኛም ተከታዮቹን በደስታ ጮቤ ያስረግጣል፤ ኢትዮጵያም በልጆችዋ ደስታ ደስ ይላታል ” ሲሉ ሰፊ ቅስቀሳ እያደረጉ ናቸው::
ከትላንት ጀምሮ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የድምፃዊው አድናቂዎች ወደ አዲስ አበባ በመግባት በዚህ ደማቅ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ለመገኘት ትኬቶቻቸውን በመቁረጥ ድግሱን ለመታደም በጉጉት እየተጠባቁ እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያ የተሰኘውን አልበሙን ለገበያ መቅረብ ተከትሎ ለበርካታ ወራት በአሜሪካና በአውሮፓ ሥራዎቹን ሲያቀርብ ቆይቶ መስከረም 5 ቀን 2011 በሚሊኒየም አዳራሽ ከዓመታት በኋላ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አድናቂዎቹን ማዝናናቱ ይታወሳል፡፡
ይህንኑ የሚሌኒየም አዳራሽ የሙዚቃ ዝግጅት በተቀነባበረ የቪዲዮ ቅንብር ለገበያ ከማብቃቱም በተጨማሪ በዩቲዩብ ቻናል በርካቶች እየተከታተሉት ይገኛሉ። ይህ የቀጥታ የቪዲዮ ቀረጻ በኢትዮጵያ ታሪክ የተዋጣለት ጥንቅር መሆኑ ይታወቃል።