ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ለ4 የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ የ4 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ውል ስምምነት ከተለያዩ ተቋራጮች ጋር መፈራረሙ ተሰማ።
በውል ስምምነቱ ላይ የተቋሙ የሥራ ሓላፊዎች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንዲሁም መንገድ ከሚገነባባቸው አካባቢዎች የተወከሉ የአገር የሽማግሌዎች ተገኝተዋል። የመንገድ ፕሮጀክቶቹ አጠቃላይ ወጪ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ነው።
በከፍተኛ ወጪ የሚገነቡት መንገዶች የቆሼ – ሚጦ – ወራቤ፣ ጋምቤላ – አቦቦ – ጎግ – ዲማ፣ የግሸን መገንጠያ እና የጎንጂ – ቆለላ መሆናቸው ተነግሯል። የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከ1 አመት እስከ 3 አመት ባለው ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ቅድመ ፕሮግራም ተቀምጦለታል።
ሁሉም መንገዶች በአስፋልት ደረጃ የሚገነቡ ሲሆን፤ አጠቃላይ ርዝመታቸውም 169 ኪሎ ሜትር መሆኑን የባለሥልጣኑ ኮሙዩኒኬሽን ዳሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ አስታውቀዋል። የመንገዶቹ ግንባታ ለመኪኖች ደህንነት ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር ከዚህ ቀደም ይወስድ የነበረውን ጊዜ በማሳጠር ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋል ነው የተባለው።