ዛሬ በአወዳይ የዶ/ር ዐቢይ ድጋፊዎች ከተቃዋሚ ደጋፊዎች ጋር ተጋጩ

ዛሬ በአወዳይ የዶ/ር ዐቢይ ድጋፊዎች ከተቃዋሚ ደጋፊዎች ጋር ተጋጩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ዛሬ ጠዋት የጠቅላይ ሚንስርት ዐቢይ መንግሥትንና ብልጽግና ፓርቲን ለመደገፍ የከተማዋ ነዋሪዎች አደባባይ የወጡ ሲሆን፤ በተቃራኒው ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትሩን መንግሥት በመቃወም፣ መፈክር እያሰሙ የወጡ ጥቂት ሰዎች እንደነበሩ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ የፖሊስ ባልደረባ  “ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን ለመደገፍ ሰዎች ሰልፍ ወጡ። ከዛ ለምን ለድጋፍ ወጣችሁ የሚሉ ሌሎች ሰዎችም መውጣት ጀመሩ። ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚያወግዝ መፈክር በማሰማት ድንጋይ መወርወር ጀመሩ” በማለት የግጭቱን አጀማመር ጠቁሞ፤ በደንጋይ ተመተው እና በዱላ ተደብድበው ጉዳት የደረሰባቸው ብዙ ሰዎች መኖራቸውንም አረጋግጧል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል የተከሰተውን ግጭት ለመበትን ፖሊስ በርካታ ጥይት ወደ ሰማይ መተኮሱን፤ በፖሊስ ኃይል በተተኮሰ ጥይት ጉዳት የደረሰበት ሰው ስለመኖሩ  ግን አስካሁን የታወቀ ነገር አለመኖሩን የሚናገረው የፀጥታ አባል ባለፉት ቀናት የአካባቢው የመንግሥት ባለስልጣናት ‘ለጠቅላይ ሚንስትሩ ድጋፋችሁን ለመግለጽ ሰልፍ ውጡ’ እያሉ ነዋሪዎችን ሲቀሰቅሱ መቆየታቸውን ገልጿል።

በዚህ መሰረት ዛሬ ጠዋት ላይ ሰዎች ለድጋፍ ሲወጡ እነሱን የሚቃወሙ ሌሎች ሰዎችም አደባባይ መውጣት ጀመሩ።

“በዚህ መካከል ከየት መጡ ሳይባል በርካታ የጸጥታ ኃይል አባላት ከተማዋን ወረው ግርግር ተፈጠረ ከዚያም ወደ ግጭት ተገባ” የሚለው የአወዳይ ከተማ ነዋሪ፤ ድጋፍ ለመስጠት አደባባይ ወጡ የተባሉት ሰዎች ወደው እና ፍቅደው ሳይሆን በደረሰባቸው ጫና ነው ይላል።

‘ለምን ያለ ፍላጎታችሁ ድጋፍ መስጠት አስፈለጋችሁ’ ከሚሉ ሰዎች ጋር መጋጨታቸውን የሚያስረዳው የአወዳይ ከተማ ነዋሪ፤ የጸጥታ ኃይሎች በሰዎች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል ሲል ፖሊስን ወንጅሏል።

ሌላው የአከባቢ ነዋሪ ግጭቱ የተከሰተው ጠቅላይ ሚንስትሩን ለመደገፍ በወጡ እና እነሱን በተቃወሙ መካከል መሆኑን አስታውቋል “መንገድ ዝግ ነበር። አሁን ላይ መኪኖች በመከላከያ እየታጀቡ ነው እያለፉ ያሉት” ሲል ያለውን ሁኔታ ያስረዳል።

በዛሬው ዕለት በከተማዋ ስለተከስተው ነገር ከአካባቢው ባለስልጣናትና ከፖሊስ ለማጣራት ቢቢሲ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ለጊዜው ሳይሳካ መቅረቱን፤ በተከሰተው ግጭት ሳቢያ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ቢነገርም በትክክል ለማረጋገጥ አለመቻሉን ዘግቧል።

LEAVE A REPLY