ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ለ21 ዓመታት በኔዘርላንድስ አቶ ሲራክ አስፋው በተባሉ ግለሰብ እጅ የቆየው ጥንታዊ ዘውድ ዛሬ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ. ም. ለኢትዮጵያ ተመለሰ።
በ18ኛው ክፍለ ዘመን እንደተሠራ የተነገረው ዘውድ፤ በኔዘርላንድስ ኤምባሲ በኩል ለኢትዮጵያ የተመለሰ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ቅርሱን ተረክበዋል። ቅርሱ ከመቐለ 16 ኪሎ ሜትር በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ከሚገኘውና ረዥም ዕድሜ ካስቆጠረው ሥላሴ ጨለቆት ቤተ ክርስትያን እንደተሰረቀ ከጥቂት ወራት በፊት ኢትዮጵያ ነገ መዘገቡ ይታወሳል።
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉጌታ ፍስሀ ዘውዱ ለተወሰነ ጊዜ በብሔራዊ ሙዝየም ቆይቶ ለጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እንደሚመለስ ጠቁመው ፤ ” ታሪካዊው የቤተ ክርስቲያን ቅርስ የተሰረቀው ከጨለቆት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ነበር። የሚመለስበትን ቀን ገና ባንወስንም በአድዋ በዓል ላይ ለማስረከብ አስበናል” ብለዋል:: ቅርሱ ነሀሴ 26፣ 1979 ዓ. ም. እንደተሰረቀ የሚናገሩት ዶ/ር ሙሉጌታ፤ ከቅርሱ ዝርፊያ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች ቢኖሩም፤ ቅርሱ በምን መንገድ ከአገር እንደወጣ እስካሁን አልታወቀም ነው ያሉት።
ቅርሱን ለ21 ዓመት በቤታቸው ያቆዩት አቶ ሲራክ ስለ ዘውዱ ለኔዘርላንድስ መንግሥት ካሳወቁ በኋላ ጉዳዩ በውጪ ጉዳይ ሚንስትር በኩል ወደ ባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ከዛም ወደ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን መመራቱን ዶ/ር ሙሉጌታ ገልጸዋል።
“ቅርሱ የጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን በፎቶ ማስረጃዎች ካረጋገጥን በኋላ እንዲመለስ ተወስኗል” ያሉት ዳይሬክተሩ ፤ የትግራይ ክልል ቅርሱ ከተሰረቀ በኋላ ለማስመለስ ደብዳቤዎች ይጻጻፍ እንደነበር እንዲሁም ቅርሱ ከመዘረፉ በፊት የነበረበትን ሁኔታ የሚያሳዩ የፎቶግራፍ ማስረጃዎች መኖራቸውንም ይፋ አድርገዋል።