ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ለዓመታት በተለያዮ ምክንያት ከሚወዷት አገራቸው ርቀው የኖሩ 76 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በፈቃደኝነት ከኬንያ መመለሳቸው ታወቀ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በፈቃደኝነት ወደ አገራቸው የተመለሱት ኢትዮጵያውያን በኬንያ ካኩማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ መሆናቸውን ገልጿል።
ስደተኞቹን የመመለስ ተግባሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በኬንያ መንግሥታት የጋራ ትብብር የሚከናወን ነው።
ትናንትና ምሽት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት 76 ስደተኞች ከሶማሌ ክልል የወጡ እና እስከ 12 ዓመታት በስደት የቆዩ መሆናቸው እና ከተመላሾቹ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ከመሆናቸው ባሻገር በስደት ተወልደው ያደጉ ልጆችም እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል።
በቀጣይም በርከት ያሉ ፈቃደኛ ስደተኞች ከካኩማ እና ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ወደ አገራቸው ይመለሳሉ ነው የተባለው።
በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የኬንያ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለዓመታት የቆዩ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ገልጾ ነበር:: በመጠለያ ጣቢያዎቹ ከ3 እስከ 40 ዓመታት የቆዩና ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፍላጎታቸውን የገለፁ 2 ሺህ 281 የሚሆኑ ስደተኞች ለአገራቸው እንዲበቁ የጉዞ ሰነዶችን እየሰጠ መሆኑንም ነው በወቅቱ ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሰረት ከካኩማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ 85 እንዲሁም ከዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ደግሞ 2 ሺህ 196 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የጉዞ ሰነድ ተዘጋጅቶላቸዋል። በካኩማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ 10 ሺህ በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ 7 ሺህ ገደማ በድምሩ 17 ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተጠልለው እንደሚገኙ በመነገር ላይ ነው።