በሀሰተኛ ትርክክቶች የታጀለው የታሪክ ትምህርት ማስተማሪያ ሞጁል ተሻሻለ

በሀሰተኛ ትርክክቶች የታጀለው የታሪክ ትምህርት ማስተማሪያ ሞጁል ተሻሻለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ለታሪክ ትምህርት ማስተማሪያነት የተዘጋጀው ሞጁል የተለያዩ የዘርፉ ምሁራን አስተያየቶች ተካተውበት ለማስተማሪያነት ዝግጁ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ ማስተማሪያ ሞጁል ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም የታሪክ ትምህርት ከቀደመው ህዝብ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነልቦናዊ ገፅታዎችን ለመረዳት እንደሚያስችል ጠቁመው ፤ የታሪክ ትምህርት ቀሪው ትውልድ ከስህተቶች ተምሮ ራሱን እንዲያርም ለማስቻል በማሰብ እንደሚሰጥም አስረድተዋል።

የተዘጋጀው ሞጁልም የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ ለዛሬ መድረሱን ያስታወሱት ሚኒስትሯ በዘርፉ ምሁራን ጠለቅ ያሉ አስተያየቶች እንደተሰጠበትም ገልጸዋል።

በተሰጠው ግብዓት መሰረት በርካታ ማሻሻያዎች እና እርማት ተደርጎበት በውይይቱ ከተሳታፊዎች የተነሱ ግብዓቶችን በማካተት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ታሪክን ለማስተማር የሚያስችል ሞጁል ይወጣልም እንደሚወጣም ፕ/ር ሂሩት ተናግረዋል።

ሞጁሉ ከዚህ ቀደም በሰባት ምዕራፍ የተከፋፈለ እና 107 ርዕሶችን በመያዝ የተዘጋጀ ሲሆን ፤ ህዳር ወር ላይ ለሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለአስተያየት ተልኮ ተታህሳስ ወር ላይ የተሰጠውን አስተያየት ለማጠናከር የሚረዳ አውደ ጥናት መካሄዱ ተገልጿል።

በመጀመሪያው ረቂቅ በሞጁሉ የተለዩ ችግሮች ሙሉ በሙሉ መታረማቸውና በተለያዩ መንገዶች የተሰበሰቡ አስተያየቶችም ተካተውበት ሞጁሉ ለተማሪዎች አቅም በሚመጥን ደረጃና ልክ መዘጋጀቱም ነው እየተገለፀ ያለው።በምሁራን ስምምነት ያልተደረሰባቸው አንዳንድ ነጥቦች በቀጣይ ጥናቶች ተረጋግጠው የሞጁሉ ሁለተኛ እትም ላይ እንደሚካተቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

የታሪክ ትምህርት ማስተማሪያ ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት በተዛነፉ ሀሰተኛ የታሪክ ትርክቶች የታጀለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ባለፈው ዓመት በተደጋሚ ሞጁሉን ለማስተካከል በተደረገው ጥረት ውስጥ በተለይም ብሔርተኛ ምሁራን መስማማት ባለመቻላቸው በትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ የነበረው የታሪክ ምሁራን ጉባዔ ባለመግባባት እስከመበተን መድረሱ አይዘነጋም::

LEAVE A REPLY