ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የመድኃኒቶችን ተዛማጅ ጉዳትና የአጠቃቀም ችግር ማቃለል የሚያስችሉ ሥድስት ማዕከላት ማቋቋሙን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ገለጸ፡፡
በአገሪቱ ከመድኃኒት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን በባለሥልጣኑ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ምርቶች ደህንነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስናቀች ዓለሙ ተናግረዋል፡፡ ከጥረቶቹ መካከል በተለያዩ አካባቢዎች የመድኃኒትን የጎንዮሽ ጉዳትና የአጠቃቀም ችግር ለማቃለል የሚሠሩ ማዕከላትን ማደራጀት ዋናው ተግባር መሆኑንም ጠቁመዋል።
አንዳንድ ጊዜም መድኃኒቶች በተገቢው መንገድ ካልተወሰዱ የመላመድ ባህሪ ስለሚኖራቸው ፈዋሽነታቸውን በማጣት የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ እና ማዕከላቱ ለችግሩ የሚሆን መፍትኄ እንደሚያቀርቡ ያመላከቱት የባለሥልጣን መ/ቤቱ ሓላፊ ፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ በሐረር፣ በሐዋሳ፣ በጎንደርና መቐለ በሚገኙ ሆስፒታሎች የተቋቋሙ 6 ማዕከላት ከጥቅምት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ መግባታቸውን አረጋግጠዋል።
ማዕከላቱ መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎች የሚያጋጥማቸውን የመድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳት እንዲያውቁ የሚያስችሉ ሲሆንከተቋቋሙ በኋላም 6 ሺህ 800 ጥቆማዎች ከኅብረተሰቡ መድረሳቸውን እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ጥቆማ የተሰጠባቸው መድኃኒቶች እንዲቀየሩ አንዳንዶቹም በተሻለ ፈዋሽ መድኃኒት እንዲቀየሩ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት እንዳያስከትሉ ከምርት ጀምሮ ተጠቃሚው ዘንድ እስከሚደርሱ ድረስ ደህንነታቸው የሚጠበቅበት ሁኔታ ላይም ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ተብሏል።