በረከት ስምኦን ጤንነታቸው ከአስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል ተባለ

በረከት ስምኦን ጤንነታቸው ከአስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ላለፉት 27 ዓመታት በተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነቶች ላይ ያገለገሉት እና  በመጥፎነታቸው የሚታወቁት አቶ በረከት ስምኦን በጠና መታመማቸው ተሰማ::

የኢሕአዴግ ቁልፍ ሰው የነበሩት በረከት መታመማቸውን የተናገሩት ባለቤታቸው፤ አስፈላጊውን ህክምና ባለማግኘታቸው ቤተሰቡ በስጋት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

አቶ በረከት ስምኦን ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ህመም ገጥሟቸው ህክምናቸውን በደቡብ አፍሪካ መከታተል የጀመሩ ቢሆንም፤ ከጥረት ኮርፖሬት ጋር ተያይዞ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በባህርዳር በመታሰራቸው ለቀዶ ህክምና የተሰጣቸው ቀጠሮ ማለፉን የተናገሩት ባለቤታቸው ወ/ሮ አሲ ፈንቴ፤ የቀድሞው የወያኔ ባለሥልጣን ጤንነታቸው በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ በእስር የቆዩት አቶ በረከት መታመማቸውን የሰሙት ከሰው መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ አሲ “ቤተሰቦቼን አላስጨንቅም” በሚል እንዳልነገሯቸው ይገልፃሉ፡፡ ከአቶ በረከት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ያስታወሱት ባለቤታቸው፤  “ጉዳዩ የክልል በመሆኑ ክልሉን አናግሩ፤ እኔ በሌላ የግል ጉዳያችሁ ላይ ችግር ከገጠማችሁ አግዛችኋለሁ” የሚል ምላሽ ከጠ/ሚኒስትሩ እንደተሰጣቸው ይፋ አድርገዋል ተባለ፡፡

ይሄን ተከትሎም ለአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች አቶ በረከትን ጨምሮ ሌሎች አብረዋቸው የተከሰሱ ግለሰቦች በነፃ እንዲሰናበቱ  መጠየቃቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ አሲ፤ የአመራሮቹ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ በረከት በፍጥነት አስቸኳይ ህክምና ካላገኙ ለህይወታቸው እንደሚያሰጋቸው የተናገሩት ወ/ሮ አሲ፤ ይህንን ጉዳይ ሁሉም በትኩረት ሊያየው የሚገባ ነው ሲሉ አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል ፡፡

LEAVE A REPLY