በኮሚሽነሩ ግድያ የተጠረጠሩ የአባ ቶርቤ አባላትና የኦነግ ወታደሮች ተያዙ

በኮሚሽነሩ ግድያ የተጠረጠሩ የአባ ቶርቤ አባላትና የኦነግ ወታደሮች ተያዙ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና ||  በቡራዮ ከተማ ትናንት በተገደሉት ኮሚሽነር ሠለሞን ታደሰ ግድያ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ አስታወቁ ።

በትናንትናው ዕለት በቡራዩ ከተማ አስተዳደር አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ሆቴል ምሳቸውን እየተመገቡ የነበሩት የከተማው ፖሊስ አዛዥ፣ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አዛዥ እንዲሁም ሌላ የፖሊስ አባልና ድምጻዊ ላይ ተኩስ ተከፍቶባቸው ኮሚሽነር ሠለሞን ሲገደሉ ሌሎቹ መቁሰላቸው  ይታወቃል።

በወንጀሉ ተጠርጥረው የተያዙት ሰዎች የቀድሞ የኦነግ ወታደሮችና በአባ ቶርቤ (ባለሳምንት) ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች እንደሆኑ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን መግለጫ አውጥቷል።

ይህንን ተከትሎም የከተማው ፖሊስና የልዩ ኃይል ፀጥታ አባላት በከተማ አስተዳደሩ አቅራቢያ የነበሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው የተሰማ ሲሆን ፤ በወንጀሉ የተጠረጠሩ ሰዎችም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው ለቢቢሲ ገልፀዋል። አቶ ጌታቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ መረጃ እንደሌላቸው እና እስካሁን ድረስ በግድያው የተጠረጠሩ ለሕግ እንዲቀርቡ አለመለየታቸውንም  ጠቁመዋል።

የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው በቡራዩ ከተማ በተደጋጋሚ የተከሰቱ ግጭቶችን በማንሳትም የከተማው የፀጥታ ኃይል መሥራት ያለበት በርካታ ሥራዎች እንዳሉ ነው የተናገሩት። በተደጋጋሚ በከተማውና በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ግጭት ሲፈጠርም “አባ ቶርቤ” የሚለው ስም በጥቅሉ እንደሚጠራ በማስታወስ በደፈናው ከመግለጽ ይልቅ ይህ ቡድኑ ማን እንደሆነና ለምን ተልዕኮ እንደተሰማራ በአግባቡ ተመርምሮ ለህዝቡ መገለጽ እንደሚኖርበትምአስታውቀዋል።

ቀደም ሲል  የኦነግ አመራሮች አባ ቶርቤ የሚባለው ቡድን ከእነርሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው በመግለጽ መናገራቸው ይታወሳል። ባለፈው ሳምንት በቡራዩ በአንድ ሆቴል ምረቃ ላይ በተፈጠረ አለመግባባትና ግጭት ድምጻውያንና ታዳሚዎች ላይ ጉዳት ደርሶ ነበር። የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ጌታቸው ባልቻ የቡራዩ ከተማ አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ሠለሞን ታደሰ የቀብር ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት ተፈጽሟል።

LEAVE A REPLY