በቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ፖሊሶች ባንዲራ ሲቀሙ ነበር፤ የገባው 150 ሺህ ሰው ተገምቷል

በቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ፖሊሶች ባንዲራ ሲቀሙ ነበር፤ የገባው 150 ሺህ ሰው ተገምቷል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የየካቲት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው ቴዲ አፍሮ ኮንሰርት በስኬት እና በሰላም ተጠናቋል። ወደ ኮንሰርቱ ሲገቡ የነበሩ ታዳሚዎችን ፖሊሶች በማስቆም ባንዲራ ሲቀሙ እንደነበርና የአዲስ አበባ ህዝብና አንዳንድ ፖሊሶች ባሳዩት ትግስት ሁከት ሳይቀሰቀስ ማለፉን ለመረዳት ተችሏል::

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ ቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ዝግጅት በመስቀል አደባባይ ትናንት ሲካሄድ 150 ሺ የሚሆኑ ሰዎች ተገኝተውበታል ተብሎም እንደሚገመት አዘጋጆቹ ተናገሩ።

የኮንሰርቱ አዘጋጅ የሆነው ላየንስ ፕሮሞሽን ዋነኛ መስራች ዲጄ አቢሲኒያ (ያይንእሸት ጌታቸው) ለቢቢሲ እንደገለፀው ምንም እንኳን የቲኬት ሽያጩ እስከ ትናንት ምሽት ድረስ የነበረ ከመሆኑ አንፃር ምን ያህል ሰው በትክክል እንደተገኘ በዛሬው እለት ለመናገር ቢያዳግትም ባለው ግምገማ ግን እስከ መቶ አምሳ ሺ የሚገመቱ ታዳሚዎች ተገኝተዋል ብሏል።

በዲጄ የሙዚቃ ዝግጅት በተጀመረው የሙዚቃ ኮንሰርት ወደ 2፡30 አካባቢ በአቡጊዳ ባንድ ታጅቦ ቴዲ አፍሮ መድረኩን የተረከበ ሲሆን፤ እስከ ሌሊቱ 6፡15 ድረስ በተለያየ ጊዜ የተጫወታቸውንና ህዝቡ እንደ ብሄራዊ መዝሙር የሚቆጥራቸውን ሙዚቃዎቹን ለአድናቂዎቹ አቅርቧል።

ህዝቡ በጩኸት፣ በደስታ፣ በጭፈራ ለአርቲስቱ ያላቸውን አድናቆት የገለጸ ሲሆን፤ ዲጄ አቢሲኒያ የምሽቱን መንፈስ “የነበረውን ስሜት ለመግለፅ ቃላት ያንሰኛል”  በማለት አስቀምጦታል።

“ሚኒልክ”፣ ‘ቀነኒሳ’ ‘አፄ ቴዎድሮስ’ ‘ጥቁር ሰው’ ፣ ‘ኢትዮጵያ’ ‘ሸ መንደፈር’ እንዲሁም ሌሎቹንም ዘፈኖቹን ግጥሞቹን የሚያውቁት ታዳሚዎቹ እኩል አብረውት መዝፈናቸው ምሽቱን የተለየ እንዳደረገው ብዙዎች በማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻቸው አስፍረዋል። በተለይም “ጃ ያስተሰርያል’ን ሲዘፍን ይደገም የሚሉ ድምፆች በርክተው ነበር።

“ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር ጉዞ” ኮንሰርትን ለመታደም ከእኩለ ቀን ጀምሮ ወደ መስቀል አደባባይ የተጓዙ በርካታ ሰዎች በፌደራል ፖሊስና ታከለ ኡማ የአዲስ አበባን ሕዝብ ለመቆጣጠር ባቋቋሙት “ተወርዋሪ ኃይል” የፖሊስ አባላት ጥምረት አረንጓዴ ቢጫ ቀዮ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን ተቀምተዋል።

የፖሊስ አባላቱ ጀግኖች እናትና አባቶቻችን የተዋደቁላትን ሰንደቅ ዓላማ ሕዝቡን ከመቀማታቸው ባሻገር በኮፊያ እና በቲሸርት ላይ የተለጠፉ የባንዲራውን ምልክት እያስላጡ ሲያስገቡ በስፍራው የተገኘው የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢ ታዝቧል::

ይህ ይሁን እንጂ እውነተኛ አገር ወዳዱ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ጥቁር ሰው የተሰኘ ተወዳጅ ዘፈኑን ሲጫወት ንጹሁን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መድረክ ላይ ይዞ በመውጣት ከጭንቅላቱ በላይ ከፍ በማድረግ ባንዲራውን በመነጠቅ የተከፋውን ሕዝብ በድፍረትና በግልጽ ክሷል:: ቴዲ አፍሮ ከዚች የነፃነት ተምሳሌት ከሆነች ሰንደቅ ዓላማ እና ከኢትዮጵያ አንድነት በላይ ምንም እንደሌለ ለመግለጽ ለበርካታ ደቂቃዎች ባንዲራውን ከፍ አድርጎ አውለብለቧል::

LEAVE A REPLY