ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ዛሬ፣ እሁድ የካቲት 15 ጠዋት ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እና ለፓርቲያቸው ድጋፋቸውን ለመስጠት ሠልፍ በወጡ ሠልፈኞች ላይ በተወረወረ ቦምብ ቢጥቂቱ 30 ሰዎች መቁሰላቸውን የአምቦ ከተማ አስተዳደር እና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ ገለጹ።
ኃላፊው አቶ ሂንሰርሙ ደለሳ እንዳሉት ቦንቡ የተወረወረው ለድጋፍ ሰልፍ በወጡ ፈረሰኞች ላይ ነው። ለብልፅግና ፓርቲና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ድጋፍ ለመስጠት ለዛሬው ሰልፍ ሲዘገጃጁ በነበሩ የአምቦ ነዋሪዎች ላይ ሰሞኑን አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኛ ድርጅቶችና ግለሰቦች ደጋፊ የሆኑ ጽንፈኞች በተለያየ መንገድ ሕዝቡን ሲያስፈራሩ እንደነበር የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ በስልክ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በቦምብ ጉዳት ካጋጠማቸው መካከል የህክምና እርዳታ ተደርጎላቸው ከሆሰፒታል የወጡ እንዳሉ ሁሉ የተለያዩ የጉዳት መጠን የደረሰባቸው መኖራቸውን ከአቶ ሂንሰርሙ ገለጻ መረዳት ተችሏል::
ከወንጀሉ ጋር ተያይዞ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን የተናገሩት ኃላፊው “በጫካ ውስጥ ታጥቆ የሚንቀሳቀስው ኃይል ወንጀሉን ሳይፈፅም እንደማይቀር እንጠረጥራለን” ብለዋል።
በጥቃቱ በርካታ ፈረሶችም መጎዳታቸውን ከአምቦ ከተማ ነዋሪዎች የተገኘው ያሳያል። ከቀናት በፊት በአወዳይ ከተማ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ድጋፋቸውን ለመግለጽ በወጡ ሰዎችና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭት አጋጥሞ ለሰልፍ በወጡ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ኢትዮጵያ ነገ መዘገቡ አይዘነጋም።
ሰሞኑን በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደርና ለአዲሱ ፓርቲያቸው፣ ብልጽግና፣ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ነዋሪዎች በተከታታይ ሰልፍ እያደረጉ ነው። በእነዚህ የድጋፍ ሰልፎች ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠማቸው ያሉት ጽንፈኛ ፖለቲከኞች እንወክለዋለን በሚሉት ሕዝብ ተገፍተው እየወደቁ በመሆናቸው የድጋፍ ሰልፎቹን ለማስተጓጎል በመንጋ ደጋፊዎቻቸው አማካይነት የተለያዮ ተግባሮችን በመፈጸም ላይ መሆናቸው በገሃድ ታይቷል።