ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲሱ የምርጫ ምዝገባ መሰረት አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማሟላት የሚገባቸውን ዝርዝር እንዳላቀረቡ በመግለጽ በአስቸኳይ እንዲያቀርቡ ድጋሚ አሳሰበ።

ምርጫ ቦርድ ከዚህ በፊት አውጥቶት በነበረው መግለጫ ፓርቲዎች በተለይ ማሟላት ከሚገባቸው የአባላት ብዛት እስከሁን አሟልተው የቀረቡት እጅግ ጥቂት የሚባሉ ብቻ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል።

መስፈርቱን በማሟላት ለምርጫ ቦርድ በማቅረብ እየታየላቸው ከሚገኙ ጥቂት ፓርቲዎች ውስጥ ሕወሓትና አረና የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ ኢዜማ፣  አብንና ኦፌኮ እስከሁን የጠቅላላ ምዝገባ ሂደቱን ያልጀመሩ መሆኑን የደረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።

ምርጫ ቦርድ ዛሬ የወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ይነበባል ፡ –

ማስታወቂያ ለፓለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ምርጫ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና በዚሁ አዋጅ መሰረት በቦርዱ አገር አቀፍ እና የክልል ፓርቲዎች ማሟላት ያለባቸው ግዴታ ለማስፈጸም የወጣው መመሪያ ቁጥር 03/2012 መሰረት የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ማሟላት የሚገባቸውን ዝርዝር ሁኔታ የሚያስረዱ ሰነዶች ማዘጋጀቱ እና ለፓርቲዎች እንዲደርሳቸው ማድረጉ ይታወሳል፡፡

እነዚህ ሰነዶች ለእያንዳንዱ ፓርቲ ከተጻፈ ደብዳቤ ጋር በአባሪነት ተያይዘው እንዲደርሳቸው ሲደረግ በደብዳቤው ላይ በግልጽ እንደሰፈረው ሟሟላት የሚገባቸውን ሁኔታዎች ሁሉ እስከ መጋቢት 03 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ አሟልተው እንዲያቀርቡ እና ምዝገባቸውን እንዲያድሱ በግልጽ በማስታወቅ ጭምር ነበር፡፡

ነገር ግን እስከአሁን ሰነዶቻቸውን ያስገቡ ፓርቲዎች ቁጥር ዝቅተኛ በመሆኑ ፓርቲዎቹ እንዲያሟሉት በዝርዝር የተገለፀላቸውን ሁኔታዎች በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ አሟልተው እንዲያቀርቡ ቦርዱ ይህንን ማስታወቂያ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል፡፡

ስለዚህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ እና ሟሟላት የሚጠበቅባቸው ዝርዝር ሁኔታዎችን የሚያስረዱ ሰነዶች የደረሳችሁ የፓለቲካ ፓርቲዊች በሙሉ በደብዳቤ በተገለጸው የጊዜ ገደብ ማለትም መጋቢት 03 ቀን 2012 ከመድረሱ በፊት ሟሟላት የሚገባቸውን በሙሉ አሟልታችሁ ምዝገባውን ስርአት እንድትጀምሩ በዚህ ማስታወቂያ ቦርዱ አጥብቆ ያሳስባል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

LEAVE A REPLY