ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሶማሊያው ፕሬዝዳናንትና እራሷን ነጻ አገር አድርጋ ካወጀችው ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት መካከል መቀራረብን ለመፍጠር እያደረጉት ያለው ጥረት እንቅፋት እንደገጠመው ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ዘገበ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጋር ሆነው የሶማሊላንድ ዋና ከተማ የሆችውን ሐርጌሳን ለመጎብኘት የነበራቸው ዕቅድም ተቃውሞ ገጥሞታል። ጋዜጣው እንደዘገበው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቀረበው የጉብኝት ሐሳብ በሶማሊያና በሶማሌላንድ አስተዳዳሪዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ዓላማ ያደረገ መሆኑን ጋዜጣው ጠቁሟል።
በሶማሊያ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰና ማዕከላዊው መንግሥት ከወደቀ በኋላ ሶማሌላንድ በሌሎች አገራት ወይም ዓለም ዐቀፋዊ ተቋማት ይፋዊ እውቅና ባታገኝም የእራሷን ነጻ መንግሥትነት በማወጅ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥትን አቋቁማለች።
በዚህ ወር መጀመሪያ አዲስ አበባ ውስጥ የተካሄደውን የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ “ፋርማጆ” እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲን በጽሕፈት ቤታቸው ጋብዘው በማገናኘት እንዲወያዮ ማድረጋቸውም ይታወቃል።
በወቅቱ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት እንደ አውሮፓዊያኑ በ1980ዎቹ ሶማሌላንድ ውስጥ ስለተፈጸመው ጭፍጨፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። የሶማሌላንዱ ፕሬዝዳንትም የቀረበውን የይቅርታ ጥያቄ የተቀበሉት ቢሆንም፤ ለአገራቸው የምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት ግን የፋራማጆ ጉብኝት ጥያቄ “ግራ አጋቢ ነው” ሲሉ ነበር የተናገሩት።
የሶማሌ ላንድ ምክትል ሚኒስትር ሊባን ዩሱፍ ኦስማን በዚህ ጉዳይ ላይ ሰጡ በተባለው ምላሽ ላይ ጉብኝቱ የማይሆን ነገር እንደሆነ ከመጠቆማቸው ባሻገር ፤ “ፋራማጆ በሶማሌላንድ ሪፐብሊክ የሚያደርጉት ጉብኝት ፈጽሞ የማይሆን ህልም ከመሆኑ በተጨማሪ የማይሳካ ዕቅድ ነው” ሲሉ በማጣጣላቸው የሰላም የኖቤል ተሸላሚው የዶክተር ዐቢይ አሕመድ የእርቅ ጥረት ከጅምሩ ከባድ እንቅፋት ገጥሞታል።