ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢሕአዴግን አፈራርሰው ለውጡን ያስቀጥልልኛል በሚል ብልፅግና የተሰኘ ፓርቲ የመሰረቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአዲሱ ፓርቲያቸው ውስጥ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የጀመሩትን የሥልጣን ሽግሽግ አጠናክረው በመቀጠል አዳዲስ ሹመት መስጠቱን ቀጥለውበታል::
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በዚህ መሰረት በዛሬው ዕለት ሁለት አዳዲስ ሹመቶችን ይፋ አድርጓል። በአዲሱ ሹመት መሰረት በቀደመው ብአዴን ውስጥ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑትና በአማራ ሕዝብ ተሟጋችነታቸው የሚታወቁት አቶ ዮሐንስ ቧያለው የሟቹ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸው አነጋጋሪ ሆኗል::
በክልሉ ሕዝብ ዘንድ በመንግሥታዊ መዋቅር የሥልጣን ሓላፊነት ላይ ካሉ ሹመኖች መሀል ተወዳጅ እንደሆኑ ከሚነገርላቸው ጥቂት የአዴፓ ሰዎች መሀል አንዱ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቧያለው ቀጣዮ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ተብሎ ሲጠበቅ በፌደራል የሓላፊነት ማዕረግ በአንድ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንትነት እንዲገቡ መደረጉ በርካታ መላ ምቶችን ከማሰንዘሩ ባሻገር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት እውነተኛ የአማራ ሕዝብ ተሟጋቾችን እየገፋ መሆኑን የሚያመላክቱ አስተያየቶች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት እየተስተዋሉ ነው።
በብአዴን/አዴፖ የነበሩ ሁነኛ የሚባሉ አመራሮች የሚሰጡት ሹመት ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳለው የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎች ከዚህ በፊትም የጄኔራል ተፈራ ማሞ እና ኮሎኔል አለበል አማረ ላይ ተግባራዊ መደረጉን በማስታወስ የተሰጠው ቦታ የሚመጥን ባለመሆኑ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መቀበል የለባቸውም ሲሉ ይሞክራሉ።
ዛሬ ይፋ በሆነው አዲስ ሹመት መሰረት፦
1. አቶ ዮሐንስ ቧያለው የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንት
2. ዶክተር አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማ ደግሞ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከጥር 14 ጀምሮ መሾማቸውን ለማወቅ ችለናል።