ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት የሚመራው ልዑክ ለ16 ሰዓታት በአስመራ ኤርፖርት ታግቶና ወደ ኤርትራ እንዳይገባ ታግዶ ወደ አዲስ አበባ መመለሱ ታወቀ፡፡ ቤተክርስትያኗ ከሚመለከተው አካል ማብራሪያ እንዲሰጣት በመግለጫዋ ጠይቃለች።
በተያያዘም በኤርትራ ተቃዋሚዎች እና የተቃዋሚ ድረገጾች በቤተክርስቲያን ያልተባለ መልእክት እንደታለፈ አድርገው የሚያቀርቡትን ገስጻለች።
በኤርትራ አስመራ የኪዳነ ምህረት ካቴድራል 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በአል እንዲገኙ የተጋዘው የልዑካን ቡድን የካቲት 14 ቀን2012 ዓ.ም አስመራ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ከደረሰ በኋላ በቪአይፒ አገልግሎት አቀባበል ከተደረገላቸውና ብዙ ሰዓት ከጠበቁ በኋላ ከበላይ በመጣ ትዕዛዝ ኤርትራ መግባት አትችሉም እንደተባሉ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ካደረጉት መግለጫ መረዳት ተችሏል፡፡
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም የተገነጠለችው ኤርትራ የካቶሊክ ቤተክርስቲያኗ ግን እስከ 2007 ድረስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳሳት ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ሥር ስትመራ መቆየቷ ይታወሳል፡፡