ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኮሮና ቫይረስ በተቀሰቀሰባት የቻይናዋ ሁቤ ግዛት ዉሃን ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ‘ወደ አገራችን እንመለስ’ ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ደብዳቤ መጻፋቸውን የተማሪዎቹ ኅብረት ፕሬዝዳንት ዘሃራ አብዱልሃዲ አስታወቀች።
በዉሃን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ኅብረት ‘ወደ አገራችን መልሱን’ የሚለውን የተማፅኖ ደብዳቤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም መላካቸውን ተናግረዋል ።
የቻይና መንግሥት በወረርሽኙ ምክንያት መውጣትም ሆነ መግባት ከከለከለባት የዉሃን ከተማ መውጣት የሚችሉበትን ሁኔታ ቢያመቻች አብዛኞቹ ተማሪዎች ወጪያቸውን ራሳቸው ሸፍነው ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደሚፈልጉ ኅብረቱ ለተማሪዎቹ አሰራጭቶት ከነበረው መጠይቅ ለማረጋገጥ ችሏል።
ምንም እንኳ የቻይና መንግሥት አስፈላጊ ነገሮችን እያቀረበላቸው ቢሆንም ተማሪዎች ከባድ የሥነ ልቦና ጫና ላይ በመሆናቸው የግድ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ለመፃፍ መገደዳቸውን ዘሃራ ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች።
በዋጆንግ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርቷን እየተከታተለች ያለች ስሟ እንዲገለፅ ያልፈለገች ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለምትኖር የምግብ አቅርቦት ቢኖራትም ከአንድ ወር በላይ በአንድ ክፍል ውስጥ በርና መስኮት ተዘግቶ በቫይረሱ ከአሁን አሁን ተያዝኩ አልተያዝኩ በሚል ከባድ የሥነ ልቦና ስቃይ ውስጥ እንዳለች አስታውቃለች።
“በቀን ሦስት ጊዜ ከሚመጣው ምግብ በየትኛው ምክንያት በቫይረሱ እያዝ ይሆን ብዬ በጣም እጨነቃለሁ። ምክንያቱም ቫይረስ ነው አይቼ ምጠርገው ነገር አደለም፤ አየሩን ይቀይርልኛል ብዬ ኤሲ አበራለሁ ፣ ብሶብኝ መስኮት ከከፈትኩ በጭንቀት ጌታ ሆይ አደራህን እያልኩ ነው” በማለት ያለችበትን ሁኔታ ለማስረዳት ጥረት አድርጋለች።
ወረርሽኙ በፈጠረው ተመሳሳይ የሥነ ልቦና ጫና ምክንያት ከቅርብ ጓደኞቻቸው ጋር እንኳ መግባባት ያቃታቸው ተማሪዎች መኖራቸውን የምትናገረው የተማሪዎቹ ኅብረት ፕሬዝዳንት ዘሃራ “የቀን ቅዥት ደረጃ የደረሱ ተማሪዎች አሉ” ስትል የችግሩን ጥልቀት ጠቁማለች።
የአንዳንዶቹ ተማሪዎች የሥነ ልቦና ችግር ህክምና ወደሚያስፈልግበት ደረጃ የደረሰ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎችን ማነጋገር ሁሉ ግድ ያለበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። በተለይም በነገሮች ይደናገጡና ይረበሹ የነበሩ ልጆች አሁን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል።
አንድ ክፍል ውስጥ አብሮት የሚኖር ጓደኛው ምን ዓይነት የሥነ ልቦና ችግር ላይ እንዳለ የጠቆመ አንድ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ “በዚህ ሳምንት ያየሁበት ነገር አብሬው የኖርኩት ጓደኛዬ አልመስል ብሎኛል። ነገሩ በጣም ሲያሳስበን ለዩኒቨርሲቲው አሳውቀናል” ሲል ኢትዮጵያውያኑ ተማሪዎች ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ ይፋ አድርጓል።
በዉሃን የተማሪዎች ኅብረት ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ደብዳቤውን የላከው ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ዕለቴ ሲሆን ደብዳቤው ለመድረሱ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማረጋገጫ እንደደረሳቸው የኅብረቱ ፕሬዝዳንት ዘሃራ ገልፃለች።
ተመሳሳይ ማረጋገጫ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ባይደርሳቸውም ደብዳቤያቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መድረሱን በሌላ መንገድ ማረጋገጣቸውንም ተማሪዋ አስረድታለች ።
ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ወደ አገራቸው ለመመለስ በተደጋጋሚ ላቀረቡት ጥያቄ መንግሥት መጀመሪያ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ምላሽ መስጠቱ አይዘነጋም ።