በዋሽንግተን የኢትዮጵያውያን ሕዳሴ ግድብ ድርድር አሳስቦናል ሲሉ ጀሲ ጃክሰን አማሪካ እጇን እንደተነሳ...

በዋሽንግተን የኢትዮጵያውያን ሕዳሴ ግድብ ድርድር አሳስቦናል ሲሉ ጀሲ ጃክሰን አማሪካ እጇን እንደተነሳ ጠይቀዋል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢትዮጵያ በዋሽንግተን የመጨረሻ ቀጠሮ ተይዞለት በነበረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቀጣይ ድርድር ላይ እንደማትሳተፍ ለአሜሪካ መግለጿ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን በድርድሩ ላይ ያላቸውን ስጋት ለመግለጽ በስቴት ዲፓርትመንት ፊት ለፊት በመገኘት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

በዋሺንግተን ከተማ ለሁለት ቀናት ሊካሂድ ታስቦ በነበረው የሦስትዮሽ የድርድር መድረክ ላይ ኢትዮጵያ የማትሳተፈው፤ ተደራዳሪ ቡድኑ በአገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ውይይት ባለማጠናቀቁ በተጠቀሰው ጊዜ በአሜሪካ በመገኘት ውይይቱን ማድረግ እንዳልተቻለ ጥሪውን ላደረገው የአሜሪካ የትሬዠሪ ቢሮ በማስተዋወቁ ስብሰባው እንደሚያካሂድ ታውቋል።

ለድርድሩ ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎች እንደተናገሩት ግብጽ የውይይቱን አቅጣጫ ከውሃ አሞላልና አለቃቅ ርዕሰ ጉዳይ በማውጣት በተለያዩ ወቅቶች ማግኘት በሚገባት የውሃ ድርሻ ላይ በማተኮሯ ሂደቱ በተፈለገው ፍጥነት ለመሄድ አልቻለም።

ግብጽ የሱዳንን ድጋፍ በመያዝ በደረቅና ድርቅ በሚያጋጥምባቸው ጊዜያት ከአባይ ወንዝ ላገኘው ይገባል ብላ ባስቀመጠችው የውሃ መጠን ላይ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችን ተቀባይነት አላገኘችም። ባለሙያዎቹ ጨምረውም በዚህ ድርድር ሱዳንና ታዛቢ የተባሉት ወገኖች ከግብጽ ፍላጎት ጎን የመቆም አዝማሚያ አሳይተዋል።

ቀደም ሲል ተደረገውን ድርድር ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስልክ ደውለው ሂደቱ በዚህኛው ድርድር መቋጫ እንደሚያገኝ ተስፋ እንዳለቸው ተናግረው ነበር። በቅርቡም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ማይክ ፖምፒዮ አዲስ አበባ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝተው ነበር።

ምንም እንኳ የመጨረሻውን ድርድር ለማድረግና ስምምነት ላይ ለመድረስ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በግድቡ ጉዳይ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት አወያይቶ ስላልጨረሰ በመድረኩ ሊሳተፍ እንደማይችል አሳውቋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ሚኒስትሮች፣ የተደራዳሪ ኮሚቴ አባላት፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ሌሎችም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ግለሰቦች ለመገናኛ ብዙሃን ዝግ በነበረው ውይይት ላይ ኢትዮጵያ በቀጣዩ የዋሽንግትን ስብሰባ እንደማትሳተፍ ስለመወሰኑ የታወቀ ነገር የለም።

በአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ አደራዳሪነት በአዲስ አበባ፣ ካይሮ፣ ካርቱም እና ዋሽንግተን ዲሲ ሲደረጉ የነበሩት ውይይቶች ያለውጤት እንዲበተኑ የሆነው የግብጽ መከራከሪያ ነጥቦች መለዋወጥ መሆኑ ተጠቁሟል።

ምንም እንኳን የሚካሄደው ውይይት በግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ እንዲሆን ኢትዮጵያ ጥረት እያደረገች ቢሆንም በግብጽ በኩል ድርድሩ የውሃ ድርሻ ላይ እንዲያተኩር ግፊት እያደረገች ነው።

በተያያዘ ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ታዛቢ ሆና ያቀረበችው አማሪካ በኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ላይ እያሳደረች ያላቸውን ተፅዕኖ በመቃወም በዋሽንግተን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። ለስቴት ዲፓርትመንት ደብዳቤ በማስገባትም አማሪካ ከኢትዮጵያ ላይ እጇን እንደተነሳ በአጽንኦት ጠይቀዋል።

የአሜሪካ መንግሥት የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በመቃወም ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ ታዋቂ አሜሪካውያን ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።

ታዋቂው የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና የጥቁሮች መብት ተሟጋች ጀሲ ጃክሰን የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት በማውገዝና ተቃውሞውን በማሰማት ላይ ከሚገኙ ሌሎች ታውቂ አሜሪካውያን ጋር በመሆን ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑ ታውቋል።

 

LEAVE A REPLY