ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የፈረንሳዩ የቴሌቪዥን ድርጅት ካናል ፕሉስ ኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን ቻናል ከፍቶ ፊልሞችን ለማሳየት የሚያስችለውን ስምምነት ከድርጅታቸው ጋር መፈራረሙን የኖላዊ ፊልም ፕሮዳክሽን ሥራ አስኪያጅ ሐኒ ወርቁ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ፊልም ፕሮዲውሰሮች ማህበር ሰብሳቢ የሆኑት ቢንያም አለማየሁ በበኩላቸው፣ ካናል ፕሉስ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የውጪ ድርጅቶችም የኢትዮጵያን ፊልሞች ለማሳየት ፍላጎት ኖሯቸው ወደ ማህበራቸው መምጣታቸውን አስታውቀዋል።
የሚከፈተው ቻናል የተመረጡ የኢትዮጵያ ፊልሞች ብቻ የሚታዩበት መሆኑን የሚናገሩት ሥራ አስኪያጇ፤ ለተወሰኑ ወራት አዳዲስ ፊልሞችን በመከራየት ለማሳየት መስማማታቸውን እና ሥምምነቱ የተለያዩ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ እንደመሆኑ ከፕሮዲውሰር ማኅበር ጋር በመሆን የሚታዩ ፊልሞችን የመምረጥ ሥራው እንደሚሠራ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ካናል ፕሉስ፣ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሰሩ ፊልሞችን ብቻ ለተወሰነ ጊዜ ለማሳየት መዋዋሉን የሚገልፁት አቶ ቢንያም፣ የሲኒማ ጊዜያቸውን ጨርሰው የወረዱ አዳዲስ ፊልሞች፣ ሌሎች የማሳያ አማራጮችን (እንደ ዩቱብ ያሉትን) ከመጠቀማቸው በፊት በቴሌቪዥን የሚቀርቡ መሆኑን ያስረዳሉ። ይህ ስምምነት የፊልም ፕሮዲውሰሮችን እንዲሁም በፊልም ሥራ ላይ የተሳተፉ አካላትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
“የሚታዩት ፊልሞች የሃገራችንን ገጽታ የሚገነቡ፣ ፊልሙ የደረሰበትን ደረጃ የሚያሳዩ ይሆናሉ” ያሉት ሥራ አስኪያጇ፤ ቻናሉ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ፊልም ብቻ እንደሚያሳይ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ፊልሞች ገቢያቸውን የሚሰበስቡት በአብዛኛው በሲኒማ ቤቶች ከሚያሳዩት ነው የሚሉት የኖላዊ ፊልም ፕሮዳክሽን ሥራ አስኪያጅ፣ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲገዙም በርካሽ ዋጋ ነበር ብለዋል።
እነዚህ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እስከዛሬ ድረስ ፊልሞቹን ሲገዙ የባለቤትነት መብቱንም አብረው እንደሚወስዱ ያስታወሱት ሥራ አስኪያጇ፤ ካናል ፕሉስ ግን ከዚህ በተለየ አዳዲስ ፊልሞችን ለስድስት ወር ብቻ የማሳየት ፈቃድ እንደሚወስድ እና የተሻለ ክፍያም እንደሚፈጽም አረጋግጠዋል።
ከስድስት ወር በኋላ ፕሮዲውሰሩ ለፈለገው ጣቢያ የመሸጥ መብት ይኖረዋል ያሉት ሐኒ “ይህንን ማስጠበቅ መቻል ትልቅ ድል ነው” በማለትም ይናገራሉ።
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ፊልሞች በተለያየ መንገድ እንደሚሸጡ እና በሲኒማ ቤቶች ማሳየት፣ በኦንላይን እንዲታይ ማድረግ፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለተወሰነ ጊዜ መብቱን ወስደው እንዲያሳዩ ማድረግ እንደሚገኙባቸው ከአሠራሩ መረዳት ተችሏል።
ይህ ሥምምነት ሁለት ዓመት መፍጀቱን የሚናገሩት አቶ ቢኒያም በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያን ፊልሞች ለኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ለማሳየት ፈልገው መምጣታቸውን ገልጸው ፤ ፊልም በተለያየ መንገድ ሊሸጥ እንደሚችልና ከሲኒማ ቤት ውጪ፣ በሲዲ፣ በዩቱብ፣ በቴሌቪዥን በመሸጥ መጠቀም እንደሚቻልም ጭምር አስረድተዋል።
የካናል ፕሉስም መምጣት ፊልም ሠሪዎቹ የተሻለ ገንዘብ ለማግኘት የሚያስችል በመሆኑ እንደ ፕሮዲውሰር ብቻ ሳይሆን እንደ ባለሙያም ትልቅ አቅም ይፈጥራል ተብሏል:: ከዚህ በፊት ባለቤትነታቸውን አሳልፈው የተሸጡ ፊልሞች በጣቢያቸው እንደማይታዩ የሚገልፁት የኖላዊ ሥራ አስኪያጅ፤ ነገር ግን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ በተለያዩ ጣቢያዎች ሲታዩ የነበሩ ካሉ ኮንትራታቸውን ከጨረሱ በጣቢያው ሊታዩ እንደሚችሉ ነው ያመላከቱት ።
ካናል ፕሉስ በኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን ቻናል ሲከፍት ኢትዮጵያዊ ስም የሚኖረው ሲሆን፤ ስምምነቱ በቴሌቪዥን ማሳየት ብቻ እንጂ ኦንላይን ሥርጭቱን እንደማይመለከተው ገልፀዋል። ኖላዊ ፊልም ፕሮዳክሽን ከተመሠረተ 10 ዓመት የሆነው ሲሆን የተለያዩ ፊልሞችንና ዘጋቢ ፊልሞችን በመሥራት ይታወቃል።
ፕሮዳክሽኑ እንደ ‘ይግባኝ’ ያሉ ፊልሞችን ፕሮዲውስ በማድረግ ለሕዝብ ዕይታ አብቅቷል። ካናል ፕሉስ ተቀማጭነቱን በፈረንሳይ ያደረገ የሚዲያ ተቋም ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ20 ሚሊየን በላይ ተከታዮች አሉት።
ካናል ፕሉስ፣ የሚዲያ እና የፊልም ኩባንያ ለኢትዮጵያ ገበያ የሳተላይት የቴሌቪዥን አገልግሎቶችን በመስጠትና ፊልሞችን ፕሮድዩስ በማድረግ ከ70 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ኢንቨስት እያደረገ ነው ሲሉ በፈረንሳይ ኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ሔኖክ ተፈራ ሻውል በሊንክዲን ገጻቸው ላይ አስታውቀው ነበር።