“ዳ/ምኒሊክ ከዛሬዎቹ መሪዎች ይበልጣሉ” ኦባንግ ሜቶ || ታምሩ ገዳ

“ዳ/ምኒሊክ ከዛሬዎቹ መሪዎች ይበልጣሉ” ኦባንግ ሜቶ || ታምሩ ገዳ

ኢትዮጵያን እና ህዝቦችን ከዛሬ አንድ መቶ አመት በፊት የመሩት ዳግማዊ ምኒሊክ ከዛሬዎቹ መሪዎች በብዙ መልኩ የተሻሉ መሪ መሆናቸውን አንድ ታዋቂ የመብት ተሟጋች ተናገሩ።

ትብብር ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ዋና ስራአስኪያጅ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑት አቶ ኦባንግ ሜቶ የአድዋን ክብረ በአልን በማስመልከት በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት “ዛሬ አገሪቱን በጎጥ እና በብሔር ከፋፍለው እናስተዳድራለን ፣እንመራለን የሚሉት ፖለቲከኞች ከዳግማዊ ምኒሊክ ጋር በምንም መልኩ ሊነጻጸሩ አይችሉም ፣ምንሊክ በብዙ ጎኑ የተሻሉ መሪ ናቸው” ብለዋል።

እንደ አቶ ኦባንግ ገለጻ የዛሬ አንድ መቶ ሀያ አራት አመት ኢትዮጵያ ልጆቿ በአድዋ ጦርነት ላይ በወራሪው የጣሊያን ጦር ላይ ድል እንዲቀዳጁ ቆራጥ አመራር የሰጡት ዳግማዊ ምኒሊክ”ታላቅ ጀግና፣ብሔራዊ መሪ ፣እውነተኛ አገር ወዳድ ፣ኢትዮጵያን በአንድነት ያጸኑ ለአገር እና ለህዝብ ታላቅ ባለውለታ”ናቸው በማለት ዘክረዋቸዋል።

የአድዋ ድልንም በተመለከተ ኦባንግ ሲገልጹት “ለብዞዎቻችን ዛሬ ለደረስንበት ማንነታችን መንገድ የጠረገ ሲሆን በሌላ ጎኑ የዚያ ድል ውጤቶች የሆነው ይህ ትውልድ ኑሮው ለምን ሊሻሻል አልችልም?፣ከአደዋ ድልስ ምን እንማራለን?፣ዛሬ ላይ ምን አይነት ሁለን አቀፍ የሆነ ዘመቻ ማካሄድ እና አድዋ መሰል ድል መቀዳጀት ይቻላልን?ብሎ ለመጠየቅ ያስገድደናል።” ብለዋል።

እንደ ታሪክ ተመራማሪ ሳይሆን አገሩን እና ህዝቡን እንደ ሚወድ ፣ፈጣሪ በሰጠው ጸጋ ሁሌም እንደሚኮራ አንድ ተራ ዜጋ በደ/ብርሃን የኒቨርስቲ ተገኝተው ስለ አድዋ ድል ቱሩፋቶች እንዲናገሩ የተጋበዙት አቶ ኦባንግ”እየአንዳንዱ ትውልድ ከአደዋ ድል በፊትም ቢሆን በቀድምት አባቶቹ መስዋትነት እና ምርጫ የተሰጠው ውርስ አለው።ለዛሬው ማንነታችን መግለጫ ምረጡ ብንባል የቱን እንመርጣለን?፣ልፕወደፊቱ የአብሮነት እሴታችንስ የትኛው መንገድን እንመርጣለን”ሲሉ አቶ ኦባንግ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያዊያን እና አፍሪካዊያን ስደተኞች ችግር በገጠማቸው ቁጥር ዘር፣ቀለም፣ጾታ ሐይማኖት ሳይገድባቸው ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመፍጠር እና እንዲፈቱ በማስደረግ በስፋት የሚታወቁት አቶ ኦባንግ “ምንም ነገር ሳይሰሩ ኢትዮጵያን እወዳለሁ፣ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነኝ፣የአደዋንም ድል አደንቃለሁ ማለት ብቻውን ተገቢ አይደለም፣እኛ ማድረግ የምንችለውን ሌላ መጥቶ እንዲያከናውንልን፣ በተስፋ ፈረስ መጋለብ አውንታዊ ስኬት አያመጣም ፣በዚህች አጭር የህይወት ዘመናችን በአክራሪ ዘረኝነት፣በወገንትኝነት ላይ የጋራ ዘመቻ እናድርግ ፣ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ከመለያየት ፈንታ አንድነትን እንስበክ “በማለት ወገናዊ ጥሪ አቅርበዋል ።

LEAVE A REPLY