ኢትዮጵያ ጥቅሜን አሳልፌ አልሰጥም ስትል ለአሜሪካ ጣልቃ ገብነት መልስ ሰጥታለች

ኢትዮጵያ ጥቅሜን አሳልፌ አልሰጥም ስትል ለአሜሪካ ጣልቃ ገብነት መልስ ሰጥታለች

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በውሃ የመሙላትና የሙከራ ሥራ ከመጀመሩ በፊት በአገራቱ መካከል ስምምነት መፈረም እንዳለበት አሜሪካ አርብ ለሊት ባወጣችው መግለጫ ማመላከቷ  ይታወቃል።

የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው ቀደም ሲል የነበረውና ግንባታው በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስ በሚለው የመርህ ስምምነት መሰረት “ግድቡን በውሃ የመሙላትና ሥራውን የመሞከር ሂደት ስምምነት ሳይደረግ መከናወን የለበትም” ብሎም ነበር።

ትናንት (ቅዳሜ) የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ማንኛውም ነገር የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥቅም በሚጠብቅ መልኩ ብቻ እንደሚከናወንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የሚነካ ድርድር እንደማይካሄድ ይፋ አድርጓል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒሰቴር የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር የታላቁን የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ሲደረግ ከነበረው ድርድር አንጻር ያወጣው መግለጫ ከፍተኛ ቅሬታ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል መፈጠሩንም ተናግረዋል።

አርብ ለሊት የወጣው የአሜሪካ መግለጫ በተፋሰሱ አገራት መካከል የተጀመረው ድርድር በቶሎ መጠናቀቅ እንዳለበት አመልክቶ፣ ግብጽ ስምምነቱን ለመፈረም ያሳየችውን ዝግጁነት አድንቋል።

በተያያዥም በኢትዮጵያ በኩል በጉዳዩ ላይ እየተካሄደ ያለውን ብሔራዊ ምክክር መግለጫው እንደሚረዳ በማመልከት፣ ምክክሩ በቶሎ ተጠናቅቆ የድርድር ሂደቱን በማጠናቀቅ በተቻለ ፍጥነት ስምምነቱ እንዲፈረም ፍላጎታቸው መሆኑን የአሜሪካው ባለስልጣን በመስሪያ ቤታቸው በኩል ያወጡት መግለጫ ያሣያል።

የካቲት 19 እና 20 ዋሽንግተን ላይ በሚደረግ ስምምነት ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ውይይት ኢትዮጵያ እያደረኩት ያለው አገራዊ ውይይትን ስላላጠናቀቅኩ መሳተፍ አልችልም ስትል ረቡዕ ዕለት በማሳወቋ ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወሳል።

በመግለጫው ላይ የአሜሪካው የገንዝብ ሚኒስትር ቴቨን ምኑቺን ከግብጽና ከሱዳን የውጭ ጉዳይና የውሃ ሃብት ሚኒስትሮች ጋር የተናጠልና የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውም ተመልክቷል። ለወራት በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲካሄድ የነበረው ድርድር በቶሎ መቋጫ እንዲያገኝ እንደምትፈልግ አሜሪካ በመግለጫው በአጽንኦት አስታውቃለች።

አሜሪካ ሦስቱ አገራት ስምምነት እስኪፈራረሙ ድረስ ከህዳሴው ግድብ ድርድር ጋር በተያያዘ ተሳትፎዋ እንደሚቀጥልም ያረጋግጣል የገንዘብ ሚኒስቴሩ መግለጫ። አሜሪካ በሥስቱ አገራት የህግና የቴክኒክ ቡድኖች የቀረቡ ሐሳቦችን መሠረት በማድረግ የስምምነት ሰነዱ እንዲዘጋጅ ነገሮችን ስታሳልጥ እንደነበር፤ ዓለም ባንክ ደግሞ በስምምነቱ ሰነድ የቴክኒክ ጉዳዮች ዙሪያ ግብአት ማድረጉንም መግለጫው ያትታል።

ኢትዮጵያ ባልተሳተፈችበት የዋሽንግተኑ መድረክ ሱዳን እና ግብፅ በተናጠል ከአሜሪካና ዓለምባንክ ጋር ባደረጉት ውይይት ስምምነቱን በሚመለከት ሐሳባቸውን አንፀባርቀዋል። አሜሪካ ባለፉት አራት ወራት የተደረጉ ተግባራት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያሉ ሁሉንም ጉዳዮች የሚዳስስ ስምምነት እንዲደረግ የሚያስችል ውጤት አምጥተዋል ብላ እንደምታምንም በመግለጫው ታይቷል።

በአሜሪካ ዋሽንግትን ዲሲ ለሁለት ቀናት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ በሚደረገው ድርድር ላይ ኢትዮጵያ እንደማትካፈል የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።

ሚኒስቴሩ የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ በታዛቢነት በሚገኙበት የካቲት 19 እና 20/2012 ዓ.ም ከሱዳን እና ግብጽ ጋር ሊካሂድ በታቀደው ቀጣይ የሦስትዮሽ ድርድር ላይ ኢትዮጵያ እንደማትገኝ ያስታወቀው፣ ተደራዳሪ ቡድን በአገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ውይይት ባለማጠናቀቁ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

LEAVE A REPLY