ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ቅዳሜ የካቲት 21/2012 በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራሮች ትላንት እሁድ አመሻሹ ላይ ከእስር መፈታታቸው ተሰማ::
የቀድሞው የኦነግ ጦር አዛዥ የነበሩት እና አሁን የሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አብዲ ረጋሳ ግን እስካሁን ያለመፈታታቸውን ፓርቲው ገልጿል።
የፓርቲው ነባር አባል የሆኑት ለሚ ቤኛ እንደተናገሩት አመራሮቹ እሁድ ማታ ታስረው ከቆዩበት በተለምዶ ሦስተኛ ተብሎ ከሚጠራው ፖሊስ ጣቢያ የተፈቱ ሲሆን “እንዲሁ ተለቀቁ እንጂ ዋስትናም ጥሩ አልተባሉም” በማለት ገልጸዋል።
” አቶ አብዲ እስካሁን ያሉበትን አናውቅም” ያሉት ለሚ በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ግዜ ጀምሮ ቤተሰብም ሆነ ጠበቃ እንዲያገኛቸው ባለመደረጉ ምክንያት ፓርቲያቸው ስጋት እንደገባው ጠቁመው፤ “አብዲ መንግስት እና ፓርቲው ባደረገው ድርድር ከኤርትራ በሰላም ለመታገል የተመለሱ ሲሆን የኦነግ ሰራዊት ዋና አዛዥ የነበሩ ናቸው። ስለዚህ የእሳቸውን ጉዳይ በቀላሉ የምናየው አይደለም” ብለዋል።
እሁድ የካቲት 22/2012 ጠዋት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ተካሂዶ የነበረው የጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ ጉባኤ ላይ ኦነግ ሳይገኝ መቅረቱን ያረጋገጡት ለሚ ለዚህም “አመራሮቻችን ታስረውብን ለማስፈታት እየተሯሯጥን ስለነበር በጉባኤው አልተሳተፍን:: ጉባኤው መንግስት እና ፓርቲዎች መካከል ውይይት ለማሰለጥ ተጀመረ እንጂ ተቋማዊ አይደለም። አሁን ባለው ሁኔታ ብዙም ለውጥ አይታይበትም፤ ከዚህ በኋላም እያየን ወይ እንሄዳለን ወይ እንቀራለን” ብለዋል።
ኦነግ ለጋዲሳው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርግ ነበር አሁንም ይህንን እንቀጥላለን፤ ነገር ግን ተቃውሞ ሲኖረን ተቃውሟችንን እናሰማለን ነው ያሉት ሓላፊው::
አብዲ ረጋሳ፣ ሚካኤል ቦረና፣ ሽጉጥ ገለታ (ዶ/ር)፣ ያዲ አብዱልሽኩር፣ ኬናሳ አያና፣ ተስፋዬ ማኮ፣ አብዱልከሪም አብዱራህማን፣ ሙሄ ራያ፣ ሶሎሞን ተሾመ፣ ደቻሳ ዊርቱ ቅዳሜ ዕለት በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።