እስከሚቀጥለው ጦርነት ድረስ || በእውቀቱ ስዩም

እስከሚቀጥለው ጦርነት ድረስ || በእውቀቱ ስዩም

ከሁለት አመት በፊት የኤፍሬም ታምሩ ልጅ ሰርግ መልስ ተጠርቼ ኩሪፍቱ ወርጄ ነበር፤ በዚያም ከድምፀ መረዋው አቀንቃኚ አብርሃም ገብረመድህን ጋራ ተገናኘሁ:: ስናወጋ ቅደመ አያቱ በአድዋ ጦርነት ወቅት ትግራይ ገብተው የቀሩ፤ የዳር አገር ሰው መሆናቸውን ተረዳሁ፤

ዝርዝሩን አልነገረኝም፤ የመረጃ ክፍተቱን በፈጠራ ሞላሁት፤

አድዋ ጦርነት ማግስት አጤ ምኒልክ ድንኳናቸው ውስጥ ሆነው ግዳይ እየተቀበሉ ያስፎክራሉ::

አንድ ጎልማሳ ተራው ደርሶ ገባ:: ጎልማሳው እንደ አጤ ምኒልክ ራሰ በራ፤ እንደ ንጉስ ተክለሃይማኖት ብስል ቀይ ነው። ጎልማሳው በግራ እጁ የጄኔራል ዳቦርሜዳን የተቆረጠ ጭንቅላት እንደ ዝኩኒ አንጠልጥሎ ይዟል። አስገራሚው ነገር ይሄ አይደለም። ከመሰንቆ በቀር ምንም አይነት የሚታይ ትጥቅ አልነበረውም።

“ ይሄንን የጥልያንን መኮንን እንዴት ገደልከው? ”

“ ይሄ ፈረንጂ በፈረስ በመሸሽ ላይ ነበር፤ እግረኛ ሰለነበረኩ ሮጨ እንደማልደርስበት አወቅሁ፤ አጅሬ ምኔ ሞኝ! ዳገት ላይ ወጣሁና አንጀት እሚበላ ዜማ በማሲንቆ ተጫወትኩ፤ የጅኒራል ዳቦርሜዳ ፈረስ ዜማየን ሲሰማ ብርብራ እንደ ጠጣ አሳ ሰክሮ ቀጥ ብሎ ቆመ! ጂኒራሉ ቢገርፈው ቢኮለኩለው ወይ ፍንክች! ተቸክሎ ቀረ፤ ወድያው ሮጨ ደረስኩና የጄኔራሉን እግር ዘርጥቼ ከፈረሱ ጣልኩት፤ እና በራሱ ሳንጃ አንገቱን እንደ ዝሃ በጠስኩለት ”

“ ግሩም እኮ ነው!! እንዲህ አይነት ነገር ሰምታችሁ ታውቃላችሁ?” አሉና ምኒልክ አጠገባቸው ያሉትን ካህናት ዞረው ቃኘት አደረጉ፤

” እንስሳት በዜማ ሃይል ከስርአታቸው መናወጣቸው ከጥንትም የታወቀ ነው:: ” አሉ አለቃ ሀሴቱ “ አባታችን ማህሌታይ ያሬድም ተእለታት እንድ ቀን በእርሻ አጠገብ ቆሞ ሲዘምር በእርሻ ላይ ተጠምደው የነበሩ በሬዎች፤ በዜማው ጣም ፈዘው ደንግዘው አልንቀሳቀስ ብለው ነበር:: በዚህ የተናደደው ገበሬም ስራየን፤ አስታጎልክብኝ ብሎ በያዘው ጅራፍ ያሬድን እንደገረፈው ተፅፎ ይገኛል” ብለው ጨመሩ::

“አሁን ምን እናድርግልህ ትፈልጋለህ?” አሉ ንጉሱ ወደ ጎልማሳው ዞረው፤

“ ጌታየ ይህንን ጥልያን ባህር ነካክተን አንተወው! እንዲሁ እንዳማረብን ቀይ ባህር አሻግረን እናባርረው፤ ድላችንን የአድዋ ድል ሳይሆን፤ የአስመራ ድል እየተባለ ሲዘከር ይኑር”

“ ሃሳብህ ጥሩ ነው፤ ግን ስንቅ የለንም፤ ሰራዊታችንም ደክሞታል በሚቀጥለው አመት ፈረሶችችንን አጠጥረን እንመለሳለን ፤ ብልጥ ሰው የያዘውን ይዞ ያለቅሳል ” አሉ ንጉሰ ነገስቱ”

“ ጃንሆይ! እንደዝያ ከሆነ እኔ እዚህ ልቆይ”

“ለምን?”

“ ከጥቂት አመታት በፊት አፄ ዮሀንስ ቱርክ ወረረን ብለው ጠርተውን ተዋግቻለሁ።  ከዝያ ቤቴ ተመልሼ በቅጡ ሳላርፍ ጥልያን መጣ ብለው እርስዎ ጠሩኝ:: አሁን ልመለስ ብል እንኳ አገሬ ለመግባት መንፈቅ አመት ይፈጅብኛል:: ገና ለገና ያገሬ ጠላት ማለቂያ የለውምና እንደ ዝሃ ዘጊ ስመላለስ አልኖርም! “

” ይሁን ! በፈቀድክበት ተቀመጥ“ አሉ ንጉሱ::

አመት አለፈ::

ዳግማይ ምኒልክ አልተመለሱም:: ጎልማሳው ጥቂት ከራርመው አንዲት ሰሜናዊት ቆንጆ አጭተው አገቡ :: ሚስቲቱም እስከሚቀጥለው ጦርነት ድረስ የባሏን የመሰንቆ መምቻ ወደ ጥጥ መንደፍያ ቀየረችው፤

LEAVE A REPLY