ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በደቡብ ክልል ለአርሶ አደሮች የሚሰራጭ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ የክልሉ መንግሥት ከኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ የወሰደው ብድር ሳይከፈል በመጠራቀሙ የብድር መጠኑ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተሰማ::
ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በብድር ሲሰራጭ የነበረው የማዳበሪያ አቅርቦት እዳ አለመክፈሉ፣ እዳው እያሻቀበ እንዲሄድ አድርጓል:: የማዳበሪያ አቅርቦት ብድሩ የክልልሉን በጀት ዋስትና በማድረግ የሚሰጥ በመሆኑ ክልሉን ለተደራራቢ ወለድ እና ሌሎች ቅጣቶች እየዳረጉት እንደሚገኝ ታውቋል::
የክልሉ የማዳበሪያ ዕዳ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብርተጨማሪ ወለድ በማስመዝገብ ላይ የሚገኝ መሆኑን ተከትሎ ክልሉ በዓመት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ዕዳ እያስተናገደ ነው:: የ2012 ዓ.ም ምርትን ሣይጨምር የክልሉ አጠቃላይ የእርሻ ማዳበሪያ የብድር ዕዳ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ሊደርስ ችሏል::
የክልሉ ግብርና ቢሮ እና የኅብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ የአርሶ አደሩን የማዳበሪያ ፍለጎት በመለየት ማዳበሪያውን ያቀርባሉ:: የደቡብ ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የገንዘብ አቅርቦቱን የሚያመቻች ሲሆን የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ደግሞ የብድር ስርጭትና አሰባሰቡን የመቆጣጠር ሓላፊነት ግዴታ እንደነበረባቸው ይታወቃል::