ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ቀጣዮን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ ሠፊ ውይይት ሲያደርጉ የቆዮት መኢአድና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ነገ በይፋ ጥምረት እንደሚፈጽሙ ታውቋል።
በእስክንድር ነጋ የሚመራው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከሲቪክ ማኅበርነት ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት ከተቀየረና ወደ ሠላማዊ ትግል ከገባ በኋላ ለቀጣዮ አገራዊ ምርጫ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማጠናከር ከተለያዮ ፓርቲዎች ጋር ቅድመ ውይይትና ድርድር ሲያካሂድ ቆይቷል::
በተመሳሳይ በአቶ ማሙሸት አማረ የሚመራው መኢአድ ኢዜማን ጨምሮ ከተለያዮ ፓርቲዎች ጥያቄዎች ቢቀርቡለትም ሐሳቦቹን ውድቅ ሲያደርግ መቆየቱን የጠቆሙ የኢትዮጵያ ነገ ታማኝ ምንጮች ፓርቲው በስተመጨረሻ ከባልደራሱ ጋር ለምርጫው በጥምረት ለመሥራት መስማማቱን አረጋግጠውልናል::
ሁለቱ ፓርቲዎች በቀጣይነት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጥምረት ለመፈጸም በድርድር ላይ መሆናቸው ተሰምቷል:: የባልደራስና የመኢአድ ጥምረት ነገ ፓርቲዎቹ በመኢአድ ጽ/ቤት ከቀኑ 5 ሰዐት ላይ በሚሰጡት መግለጫ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል::