ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ ምንም እንኳን ግፊት ቢደረግበትም ወደቻይና የሚያደርገውን በረራ እንደማያቋርጥ በድጋሚ ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም እንደተናገሩት የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመቆጣጠር ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎችን ማቋረጥ መፍትኄ እንደማይሆን ጠቁመው በቫይረሱ ምክንያት ቻይናን ማግለል ፍትሃዊ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
“የቀጥታ በረራዎችን ማቋረጥ ቫይረሱን አይገታውም፤ ምክንያቱም ተጓዦች ከቻይና ከሌሎች አገራት በኩል ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደሌሎቹ የአፍሪካ አገራት ይገባሉ። በዚህም ነው ዓለም እርስ በርሷ ተሳስራላች የሚባለው” ሲሉ መናገራቸውን የቻይናው ዢንዋ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በአሳሳቢው ኮሮና ቫይረስ ምክንያት እንደሌሎቹ አየር መንገዶች ሁሉ የገቢ መቀነስ ማጋጠሙንና በዚህም የተጓዦች ቁጥር በ20 በመቶ መቀነሱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
ስለ ጉዳዮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም ከሳምንታት በፊት በሰጡት ምላሽ “አሁን ጊዜያዊ ችግር ስላጋጠማቸው በረራ ማቋረጥ በሞራልም በሥነ ምግባርም ተቀባይነት የለውም” በማለት የተከሰተውን ችግር ለመከላከልም “ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንጂ፤ በረራዎችን ማቋረጥ ግን ካሉ አማራጮች ውስጥ አይደለም” ማለታቸው አይዘነጋም።
የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ የታንዛኒያ፣ የሞሪሺየስ፣ የማዳጋስካር፣ የሩዋንዳ፣ የሞሮኮ፣ የግብጽና የኬንያ አየር መንገዶች ወደ ቻይናና ከቻይና ወደ የአገራቸው የሚደረጉ ሁሉንም በረራዎች እንዲቋረጡ አድርገዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት እንዳስጠነቀቀው ደካማ የጤና አገልግሎት ሥርዓት ያላቸው ድሃ አገራት ወረርሽኙን ለመቋቋም አቅም የላቸውም፤ ከእነዚህ ውስጥም አብዛኞቹ የሚገኙት በአፍሪካ ውስጥ መሆኑ አሳሳቢ ነው ብሏል።
በተያያዘ ዜና የኬንያ መንግሥት ከኮሮናቫይረስ የመስፋፋት ስጋት ጋር በተያያዘ ከሰሜናዊ የጣሊያን ሁለት ከተሞች የሚመጡ በረራዎች እንዲቋረጡ አዟል። ኬንያ ይህንን እርምጃ የወሰደችው በአውሮፓ ውስጥ በርካታ ቫይረሱ የተገኘባቸው ታማሚዎች ካሉባት አገራት አንዷ ከሆነችው ጣሊያን የመጡ መንገደኞች አፍሪካ ውስጥ በበሽታው ተይዘው በመገኘታቸው መሆኑንም ገልጿል::