የደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ከዓለም የኢንተርኔት ሶሳይቲ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዮ

የደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ከዓለም የኢንተርኔት ሶሳይቲ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዮ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ከዓለም የኢንተርኔት ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት አንድሪው ሱሊቫን ጋር መወያየታቸው ታወቀ።

በውይይታቸውም ተቋማቱ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በቅንጅት መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል። ኤጀንሲው የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች እና መለኪያዎች ዓለም ዐቀፍ ይዘት እንዲኖራቸው ከኢንተርኔት ሶሳይቲው ጋር በጋራ ለመሥራት መሥራቱን የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል።

በዚህ መሠረት ኤጀንሲው በተሰጠው ተልዕኮ የሚያከውናቸው ሥራዎች ዓለም ዐቀፋዊነትን የተለባሱ እንዲሆኑ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እንደሚሠራ ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል። በሌላ በኩል በምርምር እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ላይ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ተወያይተዋል።

የመረጃና የደህንነት ኤጀንሲው የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን የበይነ መረብ ደህንነት ንቃተ ህሊና ለማሳደግ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ላይ የኢንተርኔት ሶሳይቲው አጋር ሆኖ እንደሚሠራም  ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የኢንተርኔት ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት አንድሪው  ሱሊቫን በበኩላቸው ተቋሙ በመላው ዓለም የበይነ መረብ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እና ደህንነቱን ለማስጠበቅ እንደሚሠራ ጠቁመው ፤ ኤጄንሲው በዚህ ረገድ የሚያሠራቸውን ሥራዎች ለማገዝ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የበይነ መረብ አገልግሎትን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑን ያመላከቱት ፕሬዚዳንቱ ዘርፉ ይበልጥ ጠንካራ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ መሥራት እንደሚገባ አብራርተዋል።

ከውይይቱ ጎን ለጎን ከዓለም ዐቀፍ ኢንተርኔት ሶሳይቲ በመጡ የቴክኒካል ባለሙያዎች ለኤጀንሲው ሠራተኞች በዓለም ዐቀፍ በይነ መረብ እና ደህንነት ዙሪያ ግንዛቤ ሊያዝባቸውና ጥንቃቄ ሊደረግባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ ተደርጎላቸዋል። የኢንተርኔት ሶሳይቲ ከ29 አመት በፊት በኢንተርኔት ፈጣሪዎች አማካኝነት የተመሰረተ እና በይነ መረብ በመላው ዓለም ተደራሽ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ተአማኒ እንዲሆን እየሠራ የሚገኝ ዓለም ዐቀፍ ተቋም ነው።

LEAVE A REPLY