የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በወካባ እና ተፅዕኖ ብዛት ከሽግግር መንግሥቱ መውጣት የሕወሓት መራሹ ዘመነ መንግሥት የመጀመሪያ ውድቀት ነበር። በወቅቱ ኦሕዴድን እንደ አማራጭ በማቅረብ ኦነግን ያባረረው ኢሕአዴግ ኦነግን ሕገወጥ ፓርቲ ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም።
የወቅቱ የኦሕዴድ አመራር ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) የኋላ ኋላ ከሥልጣናቸው ሲሰናበቱ ከ80 ሺሕ በላይ ኦሮሞዎች «ኦነግ ናችሁ» ተብለው ታስረው እንደነበር መናገራቸው አይረሳም። በዚያው ሰሞን ለእስር የተዳረጉት የሕወሓቱ ጉምቱ ስዬ አብርሃም ሲፈቱ «እስር ቤቱ ኦሮምኛ ይናገራል» ያሰኛቸው ይኸው ምክንያት ነበር። የያኔው የእስር ዘመቻም የተጀመረው እንዲሁ በለውጥ ተስፋ ማግስት ነውና «ታሪክ ራሱን ይደግም ይሆን?» ብለን መጨነቃችን አያስገርምም።
የኦነግ ብሶት ምንድን ነው?
ኦነግ ብሶቱን የገለጸው «በአገሪቱ ታሪክ እስከ ዛሬ ያልተፈፀመ» ግፍ እየተፈፀመብኝ ነው በማለት ነው። ይህንን መግለጫ ያወጣው የሥራ አስፈፃሚ አባላቱ በፖሊስ ውክቢያ እና ፍተሻ ከደረሰባቸው በኋላ ታስረው ስለተፈቱ ነው (ቢያንስ እስከ ትላንት ድረስ ያልተፈቱ አንድ አመራር አባል አሉ)። ይሁንና ብሶቱ ግን የተጠራቀመ ይመስላል። ምዕራብ ኦሮሚያ በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ጠንካራ መሠረት ነው። ይህ አካባቢ ትጥቅ አልፈታም ብሎ የሸፈተው የቀድሞው የኦነግ ሠራዊት ይንቀሳቀስበታል በሚል ወታደራዊ ዘመቻ እየተካሔደበት እንደሆነ ይነገራል።
በዚህም ሰበብ ኢንተርኔትና የስልክ ግንኙነቶችም ተቋርጠዋል። በዚህ የመረጃ ጨለማ ውስጥ፣ በአካባቢው ያሉ ከታጣቂው ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ፥ ግንኙነት የሌላቸውም ሲቪሎች ለጥቃት እና እንግልት እንደተጋለጡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው መግለጫ ያስረዳል። ኦነግም ደጋፊዎቼ እየተዋከቡብኝ ነው የሚል ቅሬታ አለው።
በአጭሩ ኦነግ መሠረቱን ተነጥቋል፤ አንድም በታጣቂው ቡድን፣ አልያም በመንግሥት ተፅዕኖ። የብሶቱ ምንጭም ይኸው ይመስላል። ነገር ግን መጨረሻው ይኼ ብቻ አይደለም።
ኦነግ ሊሰረዝ ይችላል
ምርጫ ቦርድ አገር አቀፍ ፓርቲዎች 10 ሺሕ፣ ክልላዊ ፓርቲዎች ደግሞ 4 ሺሕ የመሥራች አባላት ፊርማ ካላመጡ ከመዝገቤ በሁለት ወር ውስጥ እሰርዛለሁ ካለ በኋላ ትላንት ነበር ቀነ ገደቡ ላይ የደረሰው። ሆኖም ቦርዱ ትላንት ባወጣው መግለጫ ላይ ከዘረዘራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታዎች ውስጥ አንዱ “«ኦነግ የመሥራቾች ፊርማ መነጠቁን እና በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች የአባላት እስር» እንደገጠመው የሚጠቀሰው ይገኝበታል።
አቤቱታው እውነት ከሆነ በእስር እና ዘመቻው ወቅት የመሥራቾች ፊርማ ተነጥቋል ማለት ነው። ይህ ከምርጫ ቦርድ የቀድሞ ማስታወቂያ አኳያ ከመዝገብ መሠረዝ ሊያስከትል ይችላል። ገዢው ፓርቲ ብልፅግና ፓርቲን ከመሠረተ በኋላ እያሳየ ባለው የኢሕአዴግ ባሕሪ አኳያ በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ተቀናቃኝ የሚሆነውን ይህንን ፓርቲ ለማሰናበት የተሠራ ሴራ አድርጎ መጠርጠር ሰውኛ ነው። ምርጫ ቦርድ ለዚህ ምላሽ የወሰደው እርምጃ ቢኖር «ይመለከታቸዋል» ብሎ ላሰባቸው የመንግሥት አካላት ደብዳቤ ጽፎ ማብራሪያ ስጡኝ ማለት ብቻ ነው። የሚመለከታቸው አካላት ስለዚህ ድርጊት የምናውቀው ነገር የለም የሚል ማብራሪያ ቢሰጡ ምርጫ ቦርድ ኦነግን ከመሰረዝ ወዲያ ምን አማራጭ አለው?
ኦነግ የሌለበት ምርጫ?
ኦነግ ከኦሮሚያ ውጪ መልካም ሥም የለውም ብሎ መከራከር ይቻላል። በኦሮምያ ውስጥ ግን፣ በብዙኀን ኦሮሞዎች ዘንድ ከሥሙ እና ከድርጅቱ መዋቅር በላይ ዝናና ክብር ያለው ድርጅት ነው። ኦነግ ሥልጣን ይዞ ራሱን በሥራው ማስመስከር ባይችልም፣ በደርግም ይሁን በኢሕአዴግም ዘመን በተሳዳጅነት ዘመኑ ለብዙ ኦሮሞዎች ሞት ስደት እና እንግልት ሰበብ ሆኗል። በኦነግ ሥም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ያልተሸማቀቀ የኦሮሞ ቤተሰብ ማግኘት ይቸግራል ቢባል እምብዛም የተጋነነ ላይሆን ይችላል። ለዚህ ነው የኦነግ በሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ውስጥ መኖር፣ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ሽግግር ወሳኝ ቁም ነገር የሚሆነው። ኦነግ የሌለበት ምርጫ በኦሮሚያ ተቀባይነት የማግኘቱ ነገር የሕልም እንጀራ ነው።
ታሪክ ራሱን እንዳይደግም
ኦነግ ባወጣው የብሶት መግለጫ ላይ መንግሥትን አስጠንቅቋል። «እስራቱ መቆም ካልቻለ የማያባራ እሳት ይቀጣጠላል» ብሏል። ከዚህ በፊት ኦነግ የሽግግር መንግሥቱን ጥሎ ከወጣ በኋላ፥ ኦነግን ከታሪክ ገጽ ለማጥፋት ብዙ ሙከራ ተደርጓል። ነገር ግን ሥሙ እየገነነ መጥቷል። የፓርቲውን ፕሮግራም አንብበው የማያውቁ ወጣቶች ራሳቸውን በኩራት «ኦነግ ነኝ» ብለው የሚጠሩበት ዘመን ላይ እንገኛለን። ተቀናቃኝ ፓርቲን ማፈን፣ ደጋፊዎቹን ያበዛል እንጂ አያሳንስም። ለዚህ ኦነግን የሚያክል ምሣሌ የለም። ከዚህም በላይ ይህን ያክል ተወዳጅነት ያለውን ፓርቲ ከፉክክር ውጭ ለማድረግ መሥራት ጊዜያዊ ድል ሊያመጣ ቢችል እንኳን ዘላቂ ቀውስ ግን ማስከተሉ አይቀርም። ከዚህ አንፃር የኦነግ ማስጠንቀቂያ ከንቱ ጩኸት ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ለዚህ ነው የፓርቲው ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ባስቸኳይ መፈታት የሚኖርበት።