የዓድዋ ጦርነት፣ ሙስሊም የጦር አበጋዞችና ተዋጊዎች || ብሩክ አበጋዝ

የዓድዋ ጦርነት፣ ሙስሊም የጦር አበጋዞችና ተዋጊዎች || ብሩክ አበጋዝ

የዓድዋ ጦርነት፣ ሙስሊም የጦር አበጋዞችና ተዋጊዎች እንዲሁም የአንዳርጋቸው ጽጌ ሃይማኖታዊ የቀብር ሀተታ (ይኼ ጽሁፍ ጋዜጣ ላይ የወጣ ቢሆንም እናንተ ዲያስፖራና ከአዲስ አበባ ውጭ ያላችሁ ወዳጆቼ እንዳያመልጣችሁ ነው የለጠፍኩላችሁ)
_________________________________
የአድዋ ጦርነት በታሪካችን ውስጥ ታላቅ ቦታ የሚገባው ታሪካዊ ሁነት ነው፤ ምናልባትም ከአድዋ በላይ ጀግንነት የታየባቸው ሌሎች ጦርነቶች ተካሂደው ሊሆን ይችላል ነገር ግን ከእነዚህ ሁሉ ጦርነቶች አድዋ ይለያል። አድዋ ያልሰለጠነውን ጨለማውን አህጉር አፍሪካን ለማሰልጠን በሚል ያለ ህዝቦቿ ስምምነትና እውቅና የአውሮፓ የዚያ ዘመን እብሪተኛ መንግስታት አፍሪካን በሚመቻቸው መንገድ በበርሊን ኮንፈረንስ ከተከፋፈሉ በኋላ የሚፈልጉትን ለማድረግ ወደ አፍሪካ ሲመጡ፤ “አይ እኛ ኢትዮጵያውያን እናንተ እንደምታስቡት አይደለነም” የሚል መልዕክት ያስተላለፉበት ታሪካዊ ሁነት ነው።

ከዚያ በላይ አድዋ ያልተጠበቀው የሆነበት፣ የተጠበቀው የከሸፈበት፤ የሥልጣኔ መስፈርት እንደገና እንዲታይ መነሻ የሆነበት፣ እውነት በሀሰት ላይ ድል የመታበት፣ ከባርነት ይልቅ ሞት የተመረጠበት፤ እንደ በግ እንግዛችሁ ሲባሉ “እምቢ በማለት” እንደ ሰው እንሞታለን ያሉ ጀግኖች ቀደምቶቻችን ደማቸውን ያፈሰሱበት፣ አጥንታቸውን የከሰከሱበት እራሳቸውም የወዳደቁበት ነው። አድዋ ለራሱ ክብር ለሚሰጥ ለሰው ልጅ ሁሉ በባርነት ቀንበር በጉልበተኞች እግር ስር በህይወት እና በተድላ ከመኖር ይልቅ ክብር ያለው ዘላለማዊ ሞት የተሻለ እንደሆነ ታላቅ መልዕክትን ያስተላለፈ ጦርነት ነበር።

በዚህ ታላቅ ጦርነት አርሶና አርብቶ አደሩ ህዝብ በዚህ የእናት አገር ጥሪ ደግሞ ጦርነት ወቅት ደግሞ ወታደር ሆኖ እምነት ሳይለያየው ከአራቱም አቅጣጫ ተንቀሳቅሶ ዓድዋ ላይ በደምና በአጥንቱ ታሪክ ሰርቷል። ከዚህ የገበሬ ጦር ውስጥ በርካታ ሙስሊሞች በጦር አበጋዝነት እና በተራ ተዋጊነት የተሳተፉት በራስ ሚካኤል አሊ በሚመራው የወሎ ጦር እና በራስ ወሌ ብጡል በሚመራው የየጁ፣ የራያ፣ ዋዳላ ደላንታ እና የላስታ ጦር ውስጥ ነበር።

በተለያዩ ጸሀፊወች በተደጋጋሚ እንዳስተዋልነው በታላቁ የአድዋ ጦርነት ለድሉ ከፍተኛውን ድርሻ ያበረከተው በራስ ሚካኤል ዓሊ ሥር የዘመተው የፈረሰኛ ጦር ነበር። በሌላ ግንባር ሲዋጉ የተማረኩት የጠላት ወታደሮች ሳይቀር የሚወረወረውን የፈረሰኛው ጦር ሚና እጅጉን የላቀ መሆኑን ሳይዘነጉ ቃላቸውን ሰጥተዋል። በዓድዋ ጦርነት ወቅት ከንጉሠ ነገሥቱ ምኒልክ በእስከ ቀኝ በኩል ተሰልፎ የጠላትን ጦር እንዳልነበር ያደረገ እና ውሽመጣቸውን የቆረጠውም ይኸው ጦር እንደሆነ የተለያዩ ጸሀፊወች አውስተዋል። በዋናው የዓድዋ ጦርነት ዕለት ጄነራል አልበርቶኒን ሊረዳ የመጣውን በጄነራል ዳቦርሜዳ የሚመራውን ሙሉ ብርጌድ የጠላት ጦር ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር የደመሰሰው ይኼው ፈረሰኛ ሰራዊት ነው። በጦርነቱ የጄነራል ዳቦርሜዳ ሬሳ እንኴን አልተገኘም፤ ምንም ምርኮኛም አልነበረም።

ኬነዲ ሂክማን First Italo-Ethiopian War: Battle of Adwa በሚለው ሀተታው «በራስ ሚካኤል የሚመራው ታዋቂው የወሎ ፈረሰኛ ጦር እየፎከረና እየሸለለ “ያዘው፣ እጨደው፣ ፍጀው የሚል የፉከራ ድምጽ እያስተጋባ የጣልያንን ጦር ፈጀው። እህል በማጭድ እንደሚያጭድ ገበሬ የጣልያንን ወታደር አንገት በጎራዴ አጨደው። እንዲህ ባለ ሁኔታ የአሉላ እና የሚካኤል ጦር የጠላትን ጦር ደምስሶ ጀኔራል ዳቦር ሜዳን ገድሏል።» በማለት ጽፏል። ኦግስተስ ዋይልድ በበኩሉ «የተሸነፉትና በዳቦር ሜዳ ይመሩ የነበሩት የጣልያን ወታደሮች ወደ ሀውዜንና አዲቋላ ሽሽት ጀመሩ። እየሸሹ የነበሩትን እነዚህ ወታደሮች ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ ተጨማሪ የወሎ ፈረሰኛ ጦር አባላት እንዲላክላቸው ራስ አሉላ ወደ ምኒልክ መልክት ላኩ።…… በመጨረሻም ሁለም የጦር አበጋዞች ግንባር በመፍጠር ፊታቸውን ወደ አልቤርቶኒ ወደሚመራው የግራ ግምባር አዞሩ። የራስ ሚካኤልም ጦር እንዲሁ። ጥምር ጦሩ እኩለ ቀን ላይ ሙሉ በሙሉ የጣልያንን ጦር ደመሰሰ፤ ጀነራል አልቤርቶኒም ተማረከ። ጦርነቱ በግማሽ ቀን ሲጠቃለል 56ቱም የጣልያን መድፎች፣ በርካታ ከባድና ቀላለወ መትረየሶች እንዲሁም ጠመንጃወች ተማርከዋል።” በማለት ሀተታውን አስቀምጧል። እነዚህ የተማረኩት መሳሪያወች አሁን ድረስ በደሴ ሙዚየም እንደሚገኙ የታሪክ ባለሙያው ምስጋናው ታደሰ በመጽሀፉ አውስቷል። እንደሚታውቀው ይኼ ጦር Proper Wollo ከሚባለው የዛሬው ደቡብ ወሎ ክፍል የተውጣጣ በአብዛኛው የእስልምና ተከታይ የነበረ የገበሬ ወታደር ሲሆን በሙስሊም የጦር አበጋዞችም የሚመራ እና የተደራጀ ነበር።

ከእነዚህ ታዋቂወቹ የሙስሊም ጦር አበጋዞች ዋናዋናወቹ የእርቄው ገዢ የሞሀመድ ቃንቄ ልጅ ደጅ አዝማች ይመር ሞሀመድ፣ የዓሊ ቤት ገዥ ራስ በሽር፣ የኮሬብ ገዥ ደጅ አዝማች ሊበን በሽር፣ ደጃዝማች ቃሲም መሀመድ ወዘተ በጉልህ ስማቸው የሚነሳ ነው። ዓድዋ ከተካሄደ ከሁለት ዓመት በኋላ የትግራዩ ራስ መንገሻ ሲያምጽ ከራስ መኮነን ጦር ጋር ተቀናጅቶ በቀላሉ ራስ መንገሻን በቁጥጥር ሥር ያዋለው በእነ ራስ በሽር እና ፊታውራሪ ሥራህ ብዙ የሚመራው ይኼው ጦር ነበር። ከዚህ ፈረሰኛና እግረኛ በአብዛኛው ሙስሊም ከሆነ ብርጌድ ጋር በጦርነቱ አብሮ የዘመተውና የራስ ሚካዔል (በኋላ ንጉስ) ገጣሚ(አዝማሪ) የነበረው ሀሰን አማኑ በርካታ ስንኞችን ቋጥሮ ጀግኖችን አወድሷል፤ አነቃቅቷል። ዓይነ በሲሩ ሀሰን አማኑ ዛሬ ድረስ የምንሰማቸውን አብዛኛወቹን የዓድዋ ግጥሞች ያዘመረ ነው።

ዳኘው ምኒልክ ገና ከንጦጦ በቅሎው ሲሰግር
ሁሉም ተነሳ መላው ኢትዮጵያ ሳብ አለ በእግር

ማን በነገረው ለጣልያን ደርሶ
ሚካዔል መጣ ረመጥ ለብሶ

ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ

የአባ ሻንቆ አሽከር ያ ይመር ዓሊ
በደም ተነክሮ በደም ነካሪ.
(አባ ሻንቆ የራስ ሚካዔል የፈረስ ስም ነው)

እነዚህንና በርካታ የዓድዋ ግጥሞችን ያዘመረው ሀሰን አማኑ ነው። ዓድዋ የእነዚህ ጀግኖች ሁሉ ድምር ውጤት ነው።

ሌላኛው በርካታ ሙስሊሞችን ያቀፈው ጦር በእቴጌ ጣይቱ ብጡል ወንድም በራስ ወሌ ብጡል የሚመራው ብርጌድ ነው። ራስ ወሌ ብጡል ከዓድዋ ጀግኖች መካከል በቀደምትነት የሚጠቀሱና በጀግንነታቸው ስማቸው በተደጋጋሚ የሚወሳ የጦር ሰው ናቸው።

አስር ፊታውራሪ የጠመቀውን፣
የወሌ ፈረስ ጠጣው ብቻውን።

ከጠመንጃው ይልቅ ያይኑ መመልከት፣
አባ ጠጣው ወሌ የእነ ጉግሳ አባት፣
ሰላቶ አባራሪ ዳገት ለዳገት።

እየተባለ በአዝማሪ ስንኝ ተቋጥሮላቸዋል። ራስ ወሌ ከየጁ፣ ከላስታ፣ ከራያ፣ ከዋድላና ደላንታ የተውጣጣ ከ6000 በላይ ጦር ያሰለፉ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከራያና ከየጁ የተሰባሰበው በአብዛኛው ሙስሊም ነበር። በዚህ በእሳቸው ብርጌድ በልጃቸው በራስ ጉግሳ ወሌ ሥር ሆነው የሙስሊሙን ጦር የመሩት ሙስሊሞቹ የጦር አበጋዞች ሚና የማይናቅ ነበር። ከእነዚህ ሙስሊም አበጋዞች መካከል ቀኝ አዝማች ሀምዛ አበጋዝ፣ ቀኝ አዝማች ሞሀመድ በረንቶ፣ ባላምባራስ ይማም አምቡሎ፣ ፊታውራሪ ዓሊ ይማም፣ ሼኽ ሞሀመድ ሚዐዋ ወዘተ የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የዋርካው የሼኹ የአባ ጌትዬ ተወላጆች ናቸው፤ የክርስትያኖቹ የእነ ራስ ወሌ ብጡል የእነ እቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ የእነ ደጅ አዝማች አያሌው ብሩ ወዘተ የሩቅ ዘመዶች ናቸው።

ሼኽ ሞሀመድ መሸሻ የዕድሜ ባለጠጋውን የሼኽ ሞሀመድ ሚዐዋ የዓድዋ ውሎ ሲያጫውቱኝ የሚከተለውን ብለውኛል
«አባባ ሞሀመድ! ሙስሊም ጦር በመምራት በአምባላጌ፣ በመቀለ እና በዓድዋ ጦርነቶች ተካፍለዋል። ፈረሳቸው ደበላ አባ ጫጉ ይባል ነበር። ቀደም ብሎ በዓጤ ዮሀንስ የማጥመቅ ዘመቻ ጊዜ ከዓጤ ዮሀንስ አምስት አሽከሮች ጋር ተጋጥመው ከፈረሳቸው እንዳሉ በጎራዴ ሁሉንም አንጋለዋቸዋል፤ በጣም ኃይለኛ ፈረሰኛ ናቸው። እሳቸው ፈረንጅ የሚባል ነገር አይወዱም ነበር፤ በኋለኛው በማይጨው የጣልያን የ5 ዓመት ዘመን ከፊታቸው አያስቀርቡም ነበር። በመጀመሪያው የአምባላጌ ውጊያ ጀብዱ በመፈጸማቸው እና መሳሪያም መትረየስም ጭምር ማርከው ስለነበር ራስ ጉግሣ ወሌ በጣም ተደንቀውባቸዋል። በዋናው የዓድዋ የጦር ግጥሚያ ጠላት ወገግ ሲል ንጋት ላይ አጥቂ ሆኖ ጦርነት ሲጀምር እነ ራስ ጉግሣ በዋዜማው ጠጅ ሲጠጡ አምሽተው እንቅልፍ ላይ ስለነበሩ እና ጠላት ሳይታሰብ ስለመጣ ከባላምባራስ ይማም አምቡሎ ጋር ሆነው ጦሩን ግፋ በል እያሉ የጣልያንን ጦር በግንባር ቀደምትነት ተዋግተው ጀብዱ ፈጽመዋል። በዚህ በዓድዋ ውጊያም በርካታ የጦር መሳሪያ መትረየስም ጭምር ስለማረኩ ራስ ጉግሣ ይበሉ የመሳሪያ እና የሰው ምርኮዎትን ይዘው ለአባቴ ለራስ ወሌ ያቅርቡ እና ይሾሙበታል ግዛትም ይሰጠዎታል አላቸው። እሳቸው ግን እኔ ሹመት ምን ያደርግልኛል፤ አላህ የሾመኝ ይበቃኛል። አንተ ምርኮውን ወስደህ ተሾምበት፤ እኔ ነኝ የማረኩት ብለህ ተናገር» ብለው እንደመለሱለት የአባባ ሚዐዋ የረጅም ዘመን ኸዳሚ ሼኽ መሀመድ መሸሻ ነግረውኛል።

በራስ ወሌ ብጡል ጊዜ እና ከዚያ ቀደም ባለው ዘመን የጁ ውስጥ ዓሊ አሉላ የሚባል የታወቀ ወዮ ባይ (አልቃሽ) ነበር ይባላል። ከዓድዋ መልስ ራስ ወሌ ወይንዬ ላይ (ከወልዲያ ወደ ሳንቃ መስመር ያለች ቦታ) በዓድዋ ጦርነት ለተሰውት በአንድ ላይ የልቅሶ ውሎ ተደርጎ ሲለቀስላቸው። ዓሊ አሉላ ለደጅ አዝማች ደጉ አደም እና ለፊታውራሪ ዓሊ ነጎደ እንዲህ ሙሾ አወረደ አሉ
ጦር ይምጣ ጦር ይምጣ ለምን ትላላችሁ፣
እንደነ ደጉ አደም፣ እንደ ዓሊ ነጎደ ታስወስዳላችሁ።

የማከብራቸው አንዳርጋቸው ጽጌ ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር በሚል መጽሀፋቸው በዚህ ጦርነት የተሰውት እነዚህ ሙስሊም አርበኛ ተዋጊዎቻችን በእምነታቸው ምክንያት ሳይቀበሩ አጥንታቸው ተበትኖ ቀርቷል በማለት እንደሚከተለው አብራርተዋል
«ጦርነቱ በድል ከተጠናቀቀ በኋላ ትልቁ ስራ በጦር ሜዳ የተሰውትን እየሰበሰቡ በሥነ ስርዓት መቅበር ነበር። አገር ሊወሩ የመጡ የጣልያን ወታደሮችም አስከሬን ከጣልያን ወታደራዊ መሪወች ጋር በተደረገ ስምምነት ጣልያኖቹ እንዲቀብሯቸው ተደርጓል። ሌሎችም ኢትዮጲያውያን በሚያረካ መንገድ ባይሆንም እንደነገሩ በዘመኑ ሥርዓት ተቀብረዋል። በእምነታቸው የተነሳ አጥንታቸው ሰብሳቢ ያጣው በየወደቁበት ያለቀባሪ የቀሩት የእስልምና እምነት ተከታዮች እንደነበሩ ይኼ ጸሀፊ በመጽሀፉ ገልጾታል።…… እስከ ዛሬ ስለ አድዋ ሲነገረን ፣ ደማቸውነ አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ነፃነታችንን ለማስጠበቅ የወደቁ ሙስሊም ቀደምቶቻችን አስከሬን በእምነታቸው የተነሳ ቀባሪ እንዳጣ አናውቅም ነበር። በተለይ በአድዋ ተራሮች ላይ ሌላው ሁሉ ቀባሪ ሲመደብለት፤ ከጅብና ከጥንብ አንሳ የተረፈው የሙስሊም ጀግኖቻችን አጥንት በአድዋ ተራራ ላይ ተበትኖ ቀርቷል።»

አቶ አንዳርጋቸዉ ለዚህች ማጣቀሻ ያደረጉት ራይመንድ ጆናስ የተሰኘ የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ጸሀፊ እንደፈረንጆች አቆጣጠር በ2011 ያሳተመዉን «Battle of Adwa» የሚለውን መጽሀፉን ነው። ከዚህ መጽሀፍ ገጽ 286 በመጥቀስ ሙስሊሞቹ ተለይተው ሳይቀበሩ ቀርተዋል በማለት የጻፉ ቢሆንም፤ ጸሀፊው ራይመንድ ጆናስ መረጃውን ያገኘው ደግሞ በጦርነቱ ጊዜ በቦታው ያልነበረውና ጦርነቱ ከተካሄደ ከአራት ወራት በኋላ በአድዋ ያለፈውና የሟቾቹን አስከሬን በመበስበስ ላይ እያለ ወይም ከበሰበሰ በኋላ ከተመለከተው እንግሊዛዊዩ ኦግስተስ ዋይልድ ነው። ኦግስተስ ዋይልድ Modern Abyssinia በሚለው መጽሀፉ የአንድም ሙስሊም ኦሮሞ ሬሳው ሳይነሳ ከበቅሎና ፈረሶቻቸው በድን ጋር በጦርነቱ ቦታ ወድቆ እንዳየ ጽፏል። እዚህ ላይ ኦግስተስ ዋይልድ የሰወቹን በድን በማየት እንዴት ሙስሊም ኦሮሞወች እንደሆኑ ለማወቅ እንደቻለ የገለጸው ነገር የለም። አራት ወር ያለፈውን ሬሳ ፈራርሶ፣ ስጋው በአዉሬ ተበልቶ አጽሙ ነው ሊቀር የሚችለው እንጂ ጭራሽ ማንነት ለመለየትም ጭምር የሚያበቃ አይደለም፡፡

ታዲያ ይህ እንግሊዛዊ በምን መንገድ ነው የሙስሊም ኦሮሞ ሬሳ እና የክርስቲያን ሬሳ ብሎ መለየት እንደቻለ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል። ምናልባትም ዋይልድ የተመለከተውና የሙስሊም ኦሮሞወች ነው ያለው ሬሳ በቀብር ብዛትና አድካሚነት የተወሰነው ተቀብሮ የተወሰነው ሜዳው ላይ የቀረ ስለመሆኑም የሚያውቀው እና ያብራራው ነገር የለም። አቅራቢያ ባለው የአድዋ ሥላሴ በቤተክርስትያን ግቢ ውስጥም የተቀበሩ ሰወች ሬሳ በጣም ይሸት እንደነበርና በርከታ ሬሳ ደግሞ አካላቸው በጥቂቱ አፈር ለብሶ አብዛኛው የሰውነት ክፍላቸው አፈር ሳይለብስ ተገልጦ በድናቸው አብጦና ተጎልጉሎ እንዳየው እንዲሁም ጥቂት አለፍ ብሎ በሚገኝ አንድ ከለላ ላይ ደግሞ ብዙ ሬሳ ምንም አይነር ሥርአተ ቀብር ሳይፈጸም ወድቆ እንደተመለከተ ጽፏል። «The church yard was very foul-smelling, owing to the number of Abyssinians buried there after the battle of Adowa; the bodies had only a slight covering of earth over them, and many of the extermites were protruding, while in one of the deserted gate-houses several corpses remained without any attempt at interment (Augustus Wayld: Modern Abyssinia, Pp. 172)

የማከብራቸው አንዳርጋቸው ጽጌ በቁጭት ለተሞላ ሀተታቸው እንደ ማስረጃ ያቀረቡት ራይሞንድ ጆናስ በ2011 ያሳተመውን መጽሀፍ ነው። ራይመንድ ጆናስ ደግሞ ማስረጃወን ያገኘው ከላይ የጠቀስኩት እንግሊዛዊዩ ኦግስተስ ዋይልድ ነው። ኦገስተስ ዋይልድ ከላይ እንደተገለፀው የሙስሊሞቹ ብቻ ሳይሆን የክርስትያኖቹም በትክክል ቀብር ሳይፈጸምላቸው እንደቀረ በዝርዝር አስቀምጦ እያለ ራይመንድ ጆናስ ግን «በጦርነቱ ሜዳ ላይ ኢትዮጲያዊያኖች ሙስሊም ኦሮሞ ሟቾችን ለመቅበር አልተጨነቁም» ብሎ ድምዳሜ ላይ በመድረስ ያስቀመጠው ከእውነታው የራቀ ግላዊና ማስረጃ የሌለው ድምዳሜ ከመሆኑም በላይ ይህን የራይመንድ ጆናስን ሀተታ እንዳለ የወሰዱት አቶ አንዳርጋቸውም የተጋነነ፣ የተንጋደደ ስሜት የሚፈጥር ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ከኦግስተስ ዋይልድ ማብራሪያ መረዳት እንደሚቻለው ክርስትያን ሟቾችን ወደ አቅራቢያ ቤተክርስትያን በድናቸውን ቢወስዱትም በትክክል ግን ሥርአተ ቀብር አልተፈፀመላቸውም።

ሙስሊሞቹ ቤተክርስትያን ግቢ በድናቸው አለመወሰዱ ካልሆነ በቀር ጦር ሜዳ የወደቀው ሬሳም ሆነ ቤተክርስትያን ግቢ ተወስዶ ሜዳ ላይ የወደቀው ሬሳ ሁለቱም ሥርዓት ባለው መልኩ ባለመቀበሩ የተለየ ነገር ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። ለክርስትያኑ ሬሳ ትኩረት የተሰጠው ለሙስሊሙ ግን ትኩረት የተነፈገው የሚያስብልም አይደለም። ምናልባትም በአቅራቢያው ከቤተክርስትያን ይልቅ መስጊድ ቢኖር የተገላቢጦሽ መሆኑ አይቀርም ምክንያቱም ጉዳዩ ሃይማኖታዊ ነገር ነውና። በሌላ መልኩ የዘመተው ሙስሊም ኦሮሞ ብቻ እንደሆነ መግለፁና የሌላው ብሄር ሙስሊም አልዘመተም ወይስ የሌላ ብሄር ሙስሊሞች ተመርጠው ተቀብረዋል የሚል ጥያቄ ያስነሳል። እንደሚታወቀው በጦርነቱ በርካታ ቁጥር ያለው ሙስሊም ዘምቶ ነበር። ለእናት አገሩ የሞተው ሞቶ ጦርነቱን በድል ተወጥቶ ከሞት የተረፈው ሙስሊም ብዙ እንደሚሆን ምንም አያጠራጥርም። ታዲያ የተረፈው ሙስሊም ተዋጊ እንዴት የሃይማኖት ወንድሙን አልቀበረውም? መቼም እንዳይቀብር ተከልክሎ ነው አይባልም። ክርስትያኑም ቢሆን ቤተክርስትያን ግቢ ወይም እዚያው አካባቢ ሬሳው ተጣለ እንጂ ብዙው አልተቀበረም። በትክክል የተቀበሩት የተወሰኑ የጦር መሪወች ናቸው። ለምን ክርስትያኑስ በትክክል ስርአተ ቀብር አልፈፀመም? እነዚህን ሁለት ጥያቄዎች የሚመልስ ሰው የዘመኑ የጦርነት ሁኔታ የወቅቱ ይገባዋል ብዬ አስባለሁ።

በአድዋ ጦርነት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሬሳ እንዳልተቀበረ ግልጽ ነው፡፡ ከ30 ሺህ ሰው በላይ ነው የሞተው። ይኼን ሁሉ ለመቅበርም ቤተክርስትያን ግቢ ቀርቶ አንድ ሚጢጢ ከተማ አይበቃም። ምክንያቱም ጦርነቱ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በሸፈነ ቦታ ላይ እንደመሆኑ እና ከጦርነቱ ሁኔታ አንጻር ሁሉንም ቀብሮ ለመጨረስ የሚቻል እንዳልሆነ ለመረዳት አይከብድም፡፡ ሲጀመር ከአራት ወር በኋላ የበሰበሰ ሬሳ አይቶ ሙስሊምና ክርስትያን ኦሮሞና ሌላ ብሎ የጻፈው ዋይልድ እንዴት መለየት እንደቻለ እንቆቅልሽ ነው። ሙስሊሞች እሱ ከተመለከተው ቦታ ውጭ በሌሎች ቦታወች አለመቀበራቸውን በምን እንዳረጋገጠና እዚያ ድምዳሜ ላይ እንደደረሰ አልገለፀም። በአርባ ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ የተካሄደው ጦርነት ነው። ይኼን ሁሉ ቦታ ተዘዋውሮ ስላልረገጠ ሙስሊም መቀበሩንም ሆነ አለመቀበሩን ዋይልድ ሊያውቅ አይችልም። እንደሚገባኝ በዚያ ዘመን በጦርነቱ ጊዜ ሬሳ ሳይቀብሩ መጓዝ የተለመደ ይመስላል። ሬሳው ባለበት በጦርነቱ ቦታ የሚቆይ ሰው በበሽታ ሊያልቅ ይችላል። ይሁንና ሀቁ ይኼ ሆኖ እያለ አንዳርጋቸው ጽጌ ያቀረቡበት መንገድ ከአውዱ ውጭ በሆነ መልኩ ሙስሊሞች በሃይማኖቸው ምክንያት ሞተው እንኳን በቀብር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አድርጎ የዘመኑ ሰው እንዲያስብ እና የበደልና የመጠቃት ስሜት እንዲፈጥር የሚያደርግ ነው። አንዳርጋቸው እንደሚለው ለክርስትያኑ በተለየ መልኩ ቀባሪ ቢመደብለት ኖሮ ኦግስተስ ዋይልድ ቤተክርስትን ግቢ ውስጥ ሥርአተ ቀብር ሳይፈጸምለት የወደቀ ሬሳ ባልተመለከተ ነበር።

አንዳርጋቸው ጽጌ ከራይሞንድ ጆናስ በተጨማሪ ሙስሊሞች ተለይተው እንደተቀበሩ ያስረዳል በማለት እንደ ማስረጃ የተጠቀሙት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም «የሕይወቴ ታሪክ» በሚለው ኦቶባዮግራፊያቸው በገጽ 59 ላይ የተቀመጠውን ሀተታ ነው። አቶ አንዳርጋቸው ለሙስሊሞች ተለይቶ መቀበር እንደ ማስረጃ የተጠቀሙት ይኼ መጽሀፍም ጭራሽ ስለ ሙስሊምና ክርስትያን ተለይቶ መቀበርና አለመቀበር አያወራም። ሲጀመር አቶ አንዳርጋቸው በጠቀሱት ገጽ ላይ የተጻፈው ነገር የሚያወራው ከዓድዋ ጦርነት 3 ወራት ቀደም ብሎ በአምባላጌ ላይ ስለተካሄደው ጦርነት ነበር። ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ከቀብር ጋር በተያያዘ ስለ አምባላጌው ጦርነት ያሉት ነገር እንዲህ ነው «ወደ ጦርነት ሄጄ ስታኮስ መዋሌን ሰምተው ራስ ተቆጡኝ [ራስ መኮነን] ሁለተኛ ከሰፈር እንዳልወጣ እንዲያስጠብቅ፣ አቶ ሁሉምክንያት (የእልፍ አሽከሮች አለቃ) ታዘዘ። በማግስቱ ራሱ ውሎ አደረጉና የነጮችን ሬሳ ወደ ቤተክርስትያን እያስመጡ ሲያስቀብሩ ዋሉ። የኛን ሰወች አላስቀበሩም፤ በዚህ ሰው ሁለየ ተጉማማ (ተጉተመተመ)።» እንግዲህ ከዚህ ሀተታ ስለ ሙስሊምና ክርስትያን ተለያይቶ መቀበርና አለመቀበር የሚያወሳ አንድም ነገር የለም። ጸሀፊው «የኛን ሰወች» ብለው የገለጧቸው ሰወች ከሁለቱም ሃይማኖቶች ወገን መሆናቸው የሚያሻማ ነገር አይደለም።

የማከብራቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኢትዮጵያ ታሪክ ሙስሊም ወገኖቻችን መገፋታቸውን ለማስረዳት ከዚህ በተሻለ መልኩ በሌሎች አሳማኝና ትክክለኛ በሆኑ ማስረጃወች መሞገት እየቻሉ አሻሚ እና በተለያየ መልኩ ልንረዳውና ልዩነት ልንፈጥርበት የምንችለውን ሀተታ እንደ ማስረጃ አድርገው መውሰዳቸውና መጥቀሳቸው እንቆቅልሽ ሆኖብኛል። ምናልባትም ይኼን ሀተታቸውን መጽሀፋቸው በቀጣይ እንደገና ሲታተም ያስተካክሉታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሌሎች አንዳንድ የታሪክ ጸሀፊወች ደግሞ የሀገራችንን ክርስትያን ነገሥታቱን ብቻ ታሳቢ በማደርግና በመመልከት በአገራችን በርካታ ሙስሊም ማህበረሰብ መኖሩን በመዘንጋት በጣፏቸው ማስታወሻወች ይኼን የእስልምና ተከታይ የዓድዋ ዘመቻ እግረኛ እና ፈረሰኛ ጦር በዓድዋ ላይ ያደረገውን ተጋድሎ ለክርስትያን አገር የተከፈለ መስዋትነት በማለት ድሉን ለማጥበብ ይሞክራሉ። ክርስትያኑ ንጉሥ ነገሥት በማርያም እየማለ ተከተሉኝ ያለውን አዋጅ እና የዘመቻ ጥሪ ተቀብሎ የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድበው ለእናት ሀገሩ እና ለራሱ ክብር ሲል የተዋደቀው ይህ ሙስሊም የእግረኛ እና ፈረሰኛ ጦር የአገራችንን ዳይቨርስቲ ደመቅ አድርጎ ከሚያሳዩ ምንጊዜም ከማይረሱ ሁነቶች ውስጥ የሚመደብ እና ክብር የሚገባው ነው።

በዓድዋ ጦርነት የታጠቁ ሰዎች ብቻ አይደለም ያሸነፉት። ዓድዋ የጦር መሳሪያ አንጋቾች፣ የስንቅ አቀባዮች፣ የጠሎት አድራሾች፣ የውሀ ቀጅዎች፣ የምግብ አዘጋጆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እንደ ዓይነ ስውሩ ሀሰን አማኑ፣ ወይዘሮ ጻዲቄ እና ዓሊ አሉላ አይነት ገጣሚ፣ አዝማሪ እና አልቃሽና አወዳሾች በአጠቃላይ በአራቱም ማዕዘን ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተውጣጣው አርሶና አርብቶ አዳሪ ማህበረሰብ ያስገኘው ልብ የሚያሞቅ ለሌላ ትግል ወኔ እና ስንቅ የሚሆን ታላቅ ድል ነበር።

አድዋ የፀረ ቅኝግዛትና የፀረ ኢምፔሪያሊዝም ትግል በጭቁን ሀገራት ህዝቦች ሁሉ እንዲፋፋም መነሻ መድረክ የሆነ ታላቅ ጦርነት ነው፤ ምንም እንኳን አድዋ የብዙ ቀደምቶቻችንን ህይወት የቀጠፈ፣ ታላቅ ውድመትና መስዋዕትነት ያስከፈለ ቢሆንም እብሪተኞቹ የበርሊን ኮንፈረንስ ስምምነት ፈራሚ አውሮፓውያን መንግስታት እየመረራቸውም ቢሆን፣ እየጠሉትም ቢሆን፣ የማይፈልጉትም ቢሆን፣ ተገደውም ቢሆን የኢትዮጵያ ሀገራችንን እና ህዝቦቿን እንዲሁም የመንግስቷን ነጻነት እስከ ወዲያኛው እውቅና በመስጠት አጽድቀዋል። ዓድዋን የምንዘከረውም፣ የምናስታወሰውም በዚህ አውድ ነው።
————
የመጀመሪያው ምስል አንዳርጋቸው ጽጌ እንደ ማስረጃ የተጠቀሙት ራይመንድ ጆናስ እንደ ምንጭ አድርጎ የወሰደው የኦግስተስ ዋይልድ ስለ ቀብሩ ጉዳይ ያስቀመጠው ሀተታ ነው። ሁለተኛው ደግሞ አንዳርጋቸው ጽጌ ድምዳሜያቸውን ይደግፋል በማለት እንደ ተጨማሪ ማስረጃ ያቀረቡት የፊታውራሪ ተክለ ሀዋርያት ሀተታ ነው።

|| ከብሩክ አበጋዝ ገጽ የተወሰደ ||

LEAVE A REPLY