ከ1 ዓመት በፊት የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በዲዛይን ችግር ነው...

ከ1 ዓመት በፊት የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በዲዛይን ችግር ነው ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከአንድ ዓመት በፊት የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን  ለአደጋ  የተጋለጠበት ምክንያት የአውሮፕላኑ የዲዛይን ችግር እንደሆነ መርማሪዎች ለአሜሪካ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያዘጋጁት የአደጋው ረቂቅ ሪፖርት አሳየ።

የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ በረቂቅ ሪፖርቱ ላይ ቅሬታ ወይም እንዲለወጥ የሚያቀርበው ሐሳብ ካለው ዕድል እንደተሰጠው  ሮይተርስ ዘግቧል።

የቦርዱ ቃል አቀባይ ኤሪክ ዌይስ ጊዜያዊው ረቂቅ ሪፖርትን እንደተቀበሉ ቢገልጹም ድርጅታቸው ለውጥ እንዲደረግ ይጠይቅ እንደሆነ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። ቦይንግ ሪፖርቱን በተመለከተ ምላሹ ምን እንደሆነ በሮይተርስ ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱ ታውቋል።

ረቂቅ ሪፖርቱን ቀድሞ ይፋ ያደረገው ብሉምበርግ ኒውስ እንዳለው የሪፖርቱ ማጠቃለያ ስለኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ የበረራ ሠራተኞቹ አሠራርን በተመለከተ ውስን ወይም ምንም ነገር ባለማለቱ በምርመራው ላይ በተሳተፉ አንዳንድ ሰዎች ዘንድ ጥያቄን አስነስቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት በነበረው አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አደጋ በተመለከተ የተዘጋጀው ረቂቅ ሪፖርት፤ በአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍት ዌር ላይ በነበረ ችግርና በአብብራሪዎች ስህተት እንደተከሰከሰ በተነገረለት በተመሳሳዩ የኢንዶኔዢያው የላየን ኤር አውሮፕላን ሪፖርት ጋር መነጻጸሩ ተገልጿል። ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ ለመጓዝ ከአዲስ አበባ ከተነሳ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር 302 የአውሮፕላኑ ሠራተኞችን ጨምሮ 157 ሰዎች ሞተውበታል።

ከዚህ አሰቃቂ አደጋ በኋላም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ ተደርጓል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የበላይ ተቆጣታሪነት ሥር ካናዳ ሞንትሪያል በሚገኘው የአቪዬሽን ኤጀንሲ ደንብ መሠረት፤ ኢትዮጵያ አደጋውን በተመለከተ የመጨረሻውን ሪፖርት በአደጋው አንደኛ ዕለት ይፋ ማድረግ ይኖርባታል። 32 ኬንያዊያን፣ 18 ካናዳዊያን፣ 18 ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የ33 አገራት 157 ዜጎች ህይወታቸው ያለፈበትን የዚህን አደጋ አንደኛ ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጪው ማክሰኞ አስቦት እንደሚውል ከወዲሁ በመነገር ላይ ነው።

LEAVE A REPLY