ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የገቢዎች ሚኒስቴር 5 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው በኮንትሮባንድ የተያዙ አልባሳትን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማስረከቡ ተሰማ ።
ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ በሴቶች ለተመሠረቱ አራት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ነው ስጦታውን ያበረከተው።
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ፤ ተገቢውን የመንግሥትና የሕዝብ ጥቅም ሰውረው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን በሚፈፀሙ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
እንዲህ ዓይነት የኮንትሮባንድ ሥራዎች በጉምሩክ ጣቢያዎችና ኬላዎች ቁጥጥር ብቻ የሚገቱ አለመሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፥ ኅብረተሰቡ ድርጊቱ የአገርን ደህንነትና ኢኮኖሚ አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር መሆኑን በመገንዘብ ትብብሩን እንዲያጠናክርም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በሥድስት ወራት ውስጥ ብቻ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር በተከናወነ ሥራ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ምርቶች መያዛቸውን የደረሰን መረጃ ያመላክታል::