ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢትዮጵያ ጥቅሜን ይጎዳዋል ባለችውና በአሜሪካ እንደቀረበ በሚነገርለት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የስምምነት ሰነድ ላይ እንደማትፈርም ካሳወቀች በኋላ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በመግለጫ መወዛገባቸውን አጠናክረው ይዘውታል።
በተለይ የአረብ ሊግ ግብጽን የሚደግፍ የውሳኔ ሐሳብ ማውጣቱን ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ የውሳኔ ሐሳቡን ውድቅ የሚያደርግ መግለጫ አውጥታለች፤ ሱዳንም በዚሁ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሚሰጥና ጥሪ የሚያቀርብ መግለጫ አውጥታለች፤ በአንፃሩ ግብጽም ምላሽ ሰጥታለች።
ሱዳን፤ ኢትዮጵያና ግብጽ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ወደ ሚደረገው ድርድር በመመለስ ከስምምነት እንዲደርሱ ጥሪ አቅርባለች። ሱዳን የአረብ ሊግ ያቀረበውን ግብጽን የሚደግፍ የውሳኔ ሐሳብ እንደማትቀበለው ካሳወቀች በኋላ ነው ይህንን መግለጫ ያወጣችው:: በሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በወጣው መግለጫ ላይ አገራቱ ወደ ድርድሩ በመመለስ “የድርድሩን ሂደት በአሉታዊ መልኩ ከሚጎዳ ማንኛው ሁኔታ” እንዲቆጠቡ ሱዳን ጠይቃለች::
መግለጫው ባለፈው ሳምንት በአረብ ሊግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ሱዳን ያላትን ጥያቄም አብራርቷል። “በግብጽ የቀረበውና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ሱዳን ጥያቄ ያቀረበችው የሱዳን ሐሳብ ያልተጠየቀበት በመሆኑ እና እየተካሄደ ያለውን ውይይትና ድርድርን መንፍስ የሚጠቅም ባለመሆኑ ነው” ሲልም ያብራራል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ‘የአረብ ሊግ ግብጽን በመደገፍ ያወጣው ነው’ ያለውን የውሳኔ ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ እንደማይቀበለው ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ገልጾ ነበር። ሱዳን የአረብ ሊግ የውሳኔ ሐሳብን በተመለከተና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ስለሚደረገው ድርድር ትናንት ዕሁድ ያወጣችውን መግለጫ ተከትሎ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አገራቸውን ደስተኛ አለመሆኗን መግለጻቸውን ኢጂፕት ቱዴይ ዘግቧል።
ቃል አቀባዩ አህመድ ሐፊዝ በሰጡት መግለጫ ላይ ግብጽ የአረብ ሊግ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብን በተመለከተ ለሱዳን ተወካዮች ከቀናት በፊት ጀምሮ እንዲያውቁት ማድረጓንና እንደሚቀበሉት ቢገልጹም ምንም አይነት አስተያየት ለግብጽ ባለስልጣናት እንዳልሰጡ አስታውቀዋል።
ሐፊዝ እንዳሉት ሱዳን በኋላ ላይ የውሳኔ ሐሳቡን ደካማ እንዲሆን የሚያደርግ ማስተካካያ ማቅረቧንም ተናግረው ፤በሱዳን ባለስልጣናት ጥያቄ መሰረት ስሟ ከውሳኔ ሃሳቡ ሰነድ ላይ እንዲወጣ ተደርጓል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ የአረብ ሊግ በግድቡ ዙሪያ እየተደረገ ያለውን ድርድር ቁልፍ እውነታዎችን ሳያገናዝብ በውሳኔ ሃሳቡ የሰጠው ጭፍን ድጋፍ እንዳሳዘነው አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት በመግለጫው የውሳኔ ሃሳቡን እንደማትቀበል አሳውቃለች የተባለችውን የሱዳንን አቋም ያደነቀ ሲሆን፤ ከግድቡ አንጻር በተቀነባበረው የአረብ ሊግ አቋም ላይ “ሱዳን በድጋሚ ለምክንያታዊነትና ለፍትህ ያላትን አቋም አሳይታለች” ሲል አሞግሷታል።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን መግለጫ ተከትሎ በሰጠው ምላሽ እንዳለው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫን “አግባብነት የጎደለው፣ ዲፕሎማቲክ ያልሆነ እንዲሁም በአረብ ሊግንና በአባላቱ ላይ የተሰነዘረ ተቀባይነት የሌለው ጉንተላ ነው” በማለት አጣጥልታል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ አሞላልና የውሃ አለቃቀቅን በተመለከተ በዋሽንግተን፣ በአዲስ አበባ፣ ካርቱምና ካይሮ ሲካሄድ የቆየው ድርድር በፈረንጆቹ የካቲት ወር ማብቂያ ላይ ይፈረማል ተብሎ ቢጠበቅም ኢትዮጵያ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣት መጠየቋን ተከትሎ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ከኢትዮጵያ በኩል ተቃውሞ ገጥሞት ውዝግብን አስከትሏል።
ግብጽ የተዘጋጀውን የስምምነት ሰነድ ብትፈርምም አገራቱ ስምምነቱ ከመፈረማቸው በፊት ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ያለችው ግድብ የውሃ ሙሌት እንዳይጀመር የሚለው የአሜሪካን መግለጫ ጉዳዩን ውስብስብ አድርጎታል። የኢትዮጵያ ባለስልጣናትም የቀረበው ሰነድ መብታችንን የሚጋፋ ነው በማለት በይፋ ተቃውመውታል።
4.7 ቢሊዮን ዶላር ወጪን ይጠይቃል የተባለውና ከዘጠኝ ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፤ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሆነ በመጪው ዓመት በከፊል የኃይል ማመንጨት የሚጀምር ሲሆን ግንባታው በሦስት ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቅ እየተነገረለት ነው።