ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የገቢዎች ሚኒስቴር ቢሜት የተሰኘ የኤሌክትሪክ ገመድ አምራች ድርጅት በሁለት መሥራቾቹ መካከል አድርጌዋለሁ ባለው የ9oo ሺኅ ብር የድርሻ ስጦታ ላይ የጣለው የ570 ሚሊዮን ብር ግብር ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይና በጋራ ውሳኔ እንዲሰጥበት የገንዘብ ሚኒስቴር ወሰነ::
በኹለት ቱርካውያን ወንድማማቾች መካከል በተደረገ የባለቤትነት ድርሻ ዝውውር ድርጅቱ 900 ሺኅ ብር እንደሆነ ይግለፅ እንጂ የገቢዎች ሚኒስቴር ግን ድርጅቱ ያስመዘገበው ካፒታል ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ስለሆነ፤ እንዲሁም ግለሰቦቹ የዚህን አንድ አራተኛ በመሻሻጣቸው ምክንያት የስድስት መቶ ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ሽያጭ ነው ሲል ሞግቷል።
በዚህም መሠረት 30 በመቶ ወይም 190 ሚሊዮን ብር ግብር እና 190 ሚሊዮን ብር ቅጣትን ጨምሮ 570 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ሊከፍሉ ይገባል ሲል ወስኗል:: የቢሜት ኢነረጂ ቴሌኮም አምራች እና ንግድ ሓላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሞገስ ፈየራ፤ ቢሜት ያደረገው ሽያጭ ሳይሆን የባለቤትነት ዝውውር እንደሆነ ገልጸው አሠራሩ ተገቢ አይደለም በሚል ለገቢዎች ሚኒስቴር ቅሬታ ሰሚ ቦርድ ቅሬታ አቅርበው መታየቱን ተናግረዋል።
ገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ በጉዳዮ ላይ የሕግ ማብራሪያ ለመስጠት በቀረበለት ጥያቄ መሰረት በሚኒስቴር ዴኤታው ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በተፈረመ ደብዳቤ ለጊዜው የግብር ውሳኔው አፈፃፀም ታግዶ እንዲቆይ ወስኗል::