በሞረትና ጅሩ ወረዳ በፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችና የሕክምና ቡድን ላይ ጥቃት ተፈጸመ

በሞረትና ጅሩ ወረዳ በፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችና የሕክምና ቡድን ላይ ጥቃት ተፈጸመ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአማራ ክልል ሞረትና ጅሩ ወረዳ፣ እነዋሪ ከተማ ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሊሰጡ የመጡ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች የሐይማኖት ስብከት ለምን ያካሂዳሉ በሚል ጥቃት እንደደረሰባቸው የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ወደ ከተማዋ ያቀናው የሕክምና ቡድን 18 የውጪ አገር ዜጎች የተካተቱበት ከ200 በላይ አባላት ያሉት መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር ወጋየሁ ቦጋለ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ፕሬዝዳንት የሆኑት መጋቢ ይልማ ሙሉጌታ በበኩላቸው በእነዋሪ ከተማ ለ20 ዓመት የነበረ ቤተ ዕምነት ላይ ጥቃትና ዘረፋ መፈፀሙን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

መጋቢ ይልማ አክለውም ጥቃቱ የተፈፀመው በሐይማኖት አክራሪዎች ነው ያሉ ሲሆን ንብረቶች መዘረፋቸውን፣ ሦስት ሰዎች ተደብድበው ሆስፒታል እንደሚገኙና ቃጠሎ መፈፀሙን ተናግረዋል።

ዋና ኢንስፔክተር ወጋየሁ እንዳሉት የሕክምና ቡድኑ በከተማዋ ነጻ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የመጣው ባለፈው ቅዳሜ እለት ነው። ቡድኑ ከእሁድ ጀምሮ በእነዋሪ ጤና ጣቢያ በመገኘት ነፃ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ሲሆን፤ ለሕክምናው አገልግሎት ጎን ለጎን ከገጠር ቀበሌዎችና ከከተማው ለሚመጡ ተገልጋዮች የሃይማኖታዊ ስብከት ይደረግ እንደነበርም ታውቋል።

ቡድኑ የሕክምና አገልግሎቱን ሊሰጥ የመጣው ከእሁድ እስከ አርብ ድረስ ሲሆን ከጤና ጣቢያው ጎን ድንኳን በመጣል ሃይማኖታዊ ስብከት ሲያካሄዱ እንደነበር ነዋሪዎች ጠቁመዋል። የከተማው ነዋሪ ይህ ለምን ይሆናል? ብሎ ተቃውሞ ነበር ያሉት በሰሜን ሸዋ ዞን የሞረትና ጅሩ ወረዳ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሓላፊ የሆኑት አቶ ዳኜ አምታታው ፤ የሕዝቡን ቅሬታ ይዘው ስብከቱን እንዳያደርጉ ለማነጋገር መሞከራቸውን ገልጸዋል::

ኢንስፔክተሩ በበኩላቸው ሕዝቡ የሃይማኖት ስብከቱ በከተማዋ በሚገኘው የፕሮቴስታንት የእምነት ተቋም ቅጽር ግቢ ውስጥ ቢሰጥ ችግር የለብንም ማለቱን በማነሳት፤ ከጤና ጣቢያው ጎን ድንኳን ጥለው ስብከት ማካሄዳቸውና የሃይማኖት መጻሕፍት ማደላቸው ቁጣን እንደቀሰቀሰ አመልክተዋል።

ዋና ኢንስፔክተር ወጋየሁ አክለውም ከእሁድ ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ አገልግሎቱ በሰላም ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም በኋላ ግን ከገጠር ቀበሌዎችና ከከተማው ተቆጥተው የመጡ ወጣቶች በድንኳኑ እንዲሁም በሙሉ ወንጌል ቤተ እምነት ላይ የድንጋይ ድብደባና ቃጠሎ ጉዳት ማድረሳቸውን ተናግረዋል።

“የተቆጣው ሕዝብ ከቁጥጥር ውጪ ነበር የሆነው” በማለት በወቅቱ ጉዳት ሳይደርስ ችግሩን ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን አቶ ዳኜ አስረድተዋል ።

ዋነኛ ትኩረታችን የነጻ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ወደ ከተማችን የመጡ ባለሙያዎችና ባልደረቦቻቸው ምንም አይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው መከላከል ነበር፤ ያንንንም ማድረግ ችለናል ያሉት ዋና ኢንስፔክተር ወጋየሁ ቡድኑን እስከ ደብረብርሃን ድረስ አጅበው በመሸኘት እንዲሄዱ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

መጋቢ ይልማ በተፈጸመው ጥቃት ሦስት ሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ቢናገሩም ዋና ኢንስፔክተሩ ወጋየሁ ግን አንድ የጥበቃ ሠራተኛ ብቻ በድንጋይ መጎዳቱን እና ከንብረት አንጻር ስብከት ሲካሄድነበት የነበረ ድንኳን፣ እንግዶቹ ለመቆያ የሠሩት ካምፕና ልብስ እንዲሁም የሙሉ ወንጌል የቀድሞ ቢሮዎች መቃጠላቸውን  አረጋግጠዋል። ዋና ኢንስፔክተሩ አክለውም እስከአሁን ድረስ በጉዳዩ ተጠርጥሮ የተያዘ አንድም ግለሰብ እንደሌለ በመግለጽ ክትትል እያደረጉና መረጃ እያሰባሰቡ መሆኑነን አስታውቀዋል::

LEAVE A REPLY