በተባበሩት አረብ ኢምሬት በኮሮና ቫይረስ ከተጠረጠሩት ኢትዮጵያውያን አንዱ ነፃ ሆነ

በተባበሩት አረብ ኢምሬት በኮሮና ቫይረስ ከተጠረጠሩት ኢትዮጵያውያን አንዱ ነፃ ሆነ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ባሳለፍነው አርብ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በኮሮና ቫይረስ ተያዙ ከተባሉ የተለያዩ አገራት ዜጎች መካከል ሁለቱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ገልጾ ነበር። ይህንኑ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጡ ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአቡዳቢ የአምባሳደሩ ተወካይ ወ/ሮ ኑሪያ መሐመድ “እኛም እንደናንተው በሚዲያ ከመስማት ውጭ ምንም መረጃው የለንም” ማለታቸው አይዘነጋም።

ከኢትዮጵያውያኑ የጤናና ሌሎች ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ አዲስ መረጃ ስለመኖሩ የተጠየቁት  የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሚኒስትር ዲኤታ ለሆኑት ሊያ ታደሰ ፤ ሁለቱም ኢትዮጵያውያን ነዋሪነታቸውን በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ያደረጉ መሆናቸውን በማረጋገጥ አንደኛው ግለሰብ በንጉሡ የግል አውሮፕላን ውስጥ የሚሠራ የበረራ ባለሙያ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

” ከሁለቱ ኢትዮጵያውያን መካከል አንደኛው ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ መረጋገጡን ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጤና ሚኒስቴር አረጋግጠናል፤ ሁለተኛው ታማሚ ግን በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ዝርዝር መረጃ አልሰጡንም። ነገር ግን አሳሳቢ የሚባል ነገር እንዳልሆነ ገልጸውልናል” ብለዋል::

ሚኒስትር ዴኤታዋ ” የአንደኛው ኢትዮጵያዊ ሁኔታ ከባድ የሚባል አይደለም ፣ በሽታው ልክ እንደ ጉንፋን አይነት በሽታ እንደመሆኑ አብዛኛዎቹ ታማሚዎች ልክ እንደማንኛውም ጉንፋን ታማሚ ነው የሚሆኑት። ነገር ግን አንዳንዶች በሽታው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያድግባቸዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያዊው ጉንፋን ብቻ በሚባል ደረጃ ላይ ነው ያለው ማለት ነው” ሲሉም አብራርተዋል::

በዚህም መሠረት አንደኛው ኢትዮጵያዊ ከህመሙ የማገገም እድሉ እንዳለው ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል። ከቫይረሱ ነጻ እንደሆነ የተነገረው ግለሰብ ግን በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲሆን የሚያስገድደው ነገር እንደሌለና ወደ ቀድሞ ህይወቱ መመለስ እንደሚችልም ታውቋል።

ከግለሰቦቹ ማንነት ጋር በተያያዘ አንደኛው ኢትዮጵያዊ የአየር መንገድ ሠራተኛ ሲሆን ሁለተኛው ግን ኢትዮጵያዊ ከመሆኑና ነዋሪ ከመሆኑ ውጪ ሌላ መረጃ አለማግኘታቸውንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ 93 አገራት ቫይረሱ እንደተገኘ መገለጹን ተከትሎ ምናልባት በእነዚህ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለበሽታው ተጋልጠው እንደሆነ መረጃው አላችሁ ወይ የተባሉት ለሚኒስትር ዴኤታዋ ” እስካሁን ምንም የደረሰን መረጃ የለም። በየአገራቱ የሚገኙ ኤምባሲዎች ችግር ካለ ይነግሩናል፤ የጤና አታሼዎችም ይህንን በተመለከተ መረጃ ያደርሱናል። ነገር ግን ከበሽታው ጋር በተያያዘ እስካሁን ከየትኛውም ኤምባሲ መረጃ አልደረሰንም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

LEAVE A REPLY