እውቁን፣ ድንቁን፣ ሰርክ ብርቁን ወንድማችንን፣ ለሀገሩ ለወገኑ ድምፁን እና ድምፃችንን በማሰተጋባት ትክ የማይገኝለትን ጓዳችንን በሞት ተነጠቅን። በአብይ ፆም መሀል ዳግም አብያችንን አጣን!
በተገኝ ተካ ህልፈት የተሰማኝ ሀዘን መሪር ነው።
ከባልንጀሮቹ ባገኘሁት መረጃ መሰረት ተገኝ በስልሳዎቹ መጨረሻ ኢህአፓ ውስጥ ትግሉን የጀመረ ሲሆን በኋላም በሶማሌ በረሀ ውስጥ ለሶስት አመታት በእስር የማቀቀ፣ ጅቡቲ ላይ ለአመታት በስደት ቁም ስቅሉን ያዬ፣ አውስትራሊያ ከገባ በኋላም እስከ እለተ ሞቱ ድረስ በሁለገብ ትግሉ ሊታመን የማይችል ውድ ዋጋ የከፈለ የማህበረሰባችን ፈርጥ ነበር።
ተገኝን የማውቀው ገና ሜልበርን እንደመጣሁ በተሳተፍኩበት የኢሳት ልዩ ዝግጅት በአስተባባሪነት አብረን በሰራንበት ወቅት ሲሆን ከዚያች እለት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ኢትዮጲያውያን የሚሳተፉባቸውን ሁሉንም ዝግጅትች ሲመራ ነበር። በአማርኛም፣ በኦሮምኛም በእንግሊዝኛም አንደበተ ርቱኡና፣ አጭሩ ተገኝ ማይክ ከጨበጠ በኋላ መድረኩን ድንክ አድርጎ የመግዘፍ ምትሀት የነበረው ልዩ ሰው ነበር። እንዴት የታዳሚውን ስሜት ለበርካታ ሰአታት እንደሚቆጣጠር፣ እንዴት እያዋዛ የጨረታውን ከፍታ እንደሚሰቅለው ለማወቅ ባለም ዙሪያ በተደረጉት የገቢ ማሰባሰቢያዎች የታየውን የሜልበርንን ክብረወሰን ማመሳከር በቂ ነው።
የዴሞክራሲ ድጋፍ ግብረሀይሉና ኮሚኒቲው ሲያደርጓቸው በነበሩት የተቃውሞ ሰልፎች እና ስብሰባዎች እሱና ማይክ ከተገናኙ ጎራው እንዴት እንደሚደበላለቅ ድፍን ሜልበርን ምስክሬ ነው። በተለይም አንዳርጋቸው ፅጌ በተያዘ ሰሞን እንግሊዝ ቆንስላ ፊት ለፊት ሰልፍ ስናደርግ ተቀዛቅዞ የነበረው ድባብ እሱ ደርሶ ላውድስፒከሩን ሲጨብጠው እንዴት እንደተንቀለቀለ፣ በመፈክር፣ በለቅሶና በኡኡታም ጭምር እሪታችን እንዴት እንደተስተጋባ ሳስበው የዚህ ሰው ጨውነት የዚህ ሰው ቅመምነት ውልብ ይልብኛል። ተገኝ በቀላሉ የሚዋሀዱት፣ ሳይደክሙ የሚቀርቡት ጨዋታ አዋቂ፣ ትሁትና ቀና ሰው ነበር።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ጨምሮ በርካታ ታላላቅ ኢትዮጲያዊያንን በመጋበዝ እና ክብር በመስጠት ተግባራት ላይ የተገኝ አበርክቶ እጅግ የላቀ እንደነበር የአደባባይ እውነት ነው። ሺዎች በታደሙበት እና በመላው አለም በቀጥታ ስርጭት በተላለፈው “እንደመር በሜልበርን” በሚል መሪ ቃል የዴሞክራሲ ድጋፍ ቡድኑ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ በተገኝ የመድረክ መሪነት ሚና አለመደመም የሚቻል አይደለም።
ተገኝ የዴሞክራሲ ድጋፍ ቡድኑ የጀርባ አጥንት ከነበሩት አገር ወዳዶች አንዱ ሲሆን ኮሚኒቲውን ደም ሰጥተው ለዛሬ ካበቁት ጥቂት ኢትዮጲያዊያን የሚመደብ ነው።
ተገኝ በሜልበርን ኢትዮጲያዊያን ዘንድ የሚከበር፣ የሚወደድ የነካው ሁሉ የሚጣፍጥለት፣ የተናገረው ሁሉ የሚዋጣለት እዚህም እዚያም ሳይረግጥ ውሀ ልኩን ጠብቆ ላመነበት በፅናት የሚራመድ ኢትዮጲያዊ እንደነበር እመሰክራለሁ። በዘውግ ሳይከለል በድርጅት ሳይታጠር ኢትዮጲያዊነት ባለበት ሁሉ በቅንነት ላበረከታቸው ተግባራት ሁሉ አድናቆቴ ፍፁም ነው።
በዚህ ሰው ህልፈት ከፍተኛ ሀዘን ላይ ላላችሁ የቤተሰብ አባላት፣ ለዲሞክራሲ ድጋፍ ቡድን አባላትና በሜልበርን ለምትገኙ ኢትዮጲያዊያ በሙሉ መፅናናትን እመኛለሁ።
የወንድማችንን ነብስ ይማር!