ኃይሌ ገብረ ስላሴ ኮሮና ቫይረስ ቢዝነሴንና አትሌቲክስን እየጎዳ ነው አለ

ኃይሌ ገብረ ስላሴ ኮሮና ቫይረስ ቢዝነሴንና አትሌቲክስን እየጎዳ ነው አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከኮሮናቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ የስፖርት ውድድሮችን ጨምሮ የንግድ ዘርፉ ላይ ተጽዕኖን እያሳደረ መሆኑን የዓለማችን ታዋቂ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ተናገረ።

በ10 ሺህ ሜትር ውድድር የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያዊው ኮከብ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ወረርሽኙ በሩጫው ዘርፍና በንግድ ሥራው ላይ እያስከተለ ያለውን ጫና በተመለከተ እንደተናገረው ውድድሮች እየተሰረዙ፣ የንግድ ሥራዎችም እየተስተጓጎሉ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።

በተለያዩ ቦታዎች ሊካሄዱ የነበሩ የሩጫ ውድድሮች ወረርሽኙ በፈጠረው ስጋት ሳቢያ ሲሰረዙ በተወዳዳሪዎች ላይ ከባድ ተጽእኖን እንደሚያሳድርም ተናግሯል። “እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አዳዲስና ተስፋ ያላቸው፣ እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ሲዘጋጁ የነበሩትን ሯጮችን ብታናግሩ ውድድሮች በመሰረዛቸው የገጠማቸውን የልብ ስብራት መረዳት ትችላላችሁ።” በማለት እውነታውን ለማሳየት ሞክሯል::

ኃይሌ ገብረሥላሴ እንደሚለው ቻይና ውስጥ ብቻ በየዓመቱ ከ350 በላይ የማራቶን ውድድሮች ይካሄዳሉ። ከኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ሁሉም በቻይና የሚደረጉ የማራቶን ውድድሮች ተሰርዘዋል።

በአውሮፓም ውስጥ እንዲሁ በፈረንሳይ የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮን ሺፕ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ጠቁሞ፣ የፓሪስና የሮም ማራቶን መሰረዛቸውን ከመግለጹ ባሻገር፤ “በርካታ ውድድሮች በበሽታው መስፋፋት ምክንያት ብቻ ተሰርዘዋል፤ አልያም ወደሌላ ጊዜ ተሸጋግረዋል” ብሏል።

“አስቡት ለረጅም ጊዜ ልምምድና ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተው በድንገት ቻይና ውስጥ ውድድር አይደረግም፣ አውሮፓና አሜሪካ ውስጥ ውድድር አይኖርም ሲባል በጣም ከባድ ነገር ነው” ያለው ኃይሌ ገብረ ስላሴ “እንደ ቀደምት ሯጭነቴ ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ፤ ረጅም ጊዜ የፈጀ ዝግጅት ካደረግኩ በኋላ ውድድሩ ቢሰረዝ በጣም ልብን የሚሰብር ነገር ነው።” ሲል ለአትሌቶቻችን ያለውን ተቆርቋሪነት አሳይቷል::

የበሽታው መዛመት ስፖርትን ብቻ ሳይሆን ንግድንም እየጎዳው መሆኑን በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማራው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ተናግሯል:: ” ኪሳራው እያጋጠመ ያለው በቻይናና በአውሮፓ ውስጥ ብቻ ሳይሆን እዚህ ኢትዮጵያ የእኔን ኪስም እየነካው ነው” ሲል ብሶቱን አስተጋብቷል።

“የንግድ ሥራዬን በተመለከተም ከቻይና ያዘዝኳቸው ኮንቴይነሮች እዚያው ቆመዋል። አዳማ ውስጥ ሆቴል ለመክፈት እየተዘጋጀሁ ነበር፤ ነገር ግን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ቻይና ውስጥ ሥራ ስለሌለ ሥራዬ ተስተጓጉሏል” የሚለው ኃይሌ በሥራ ላይ ባሉት ሆቴሎቹ ውስጥም የእንግዶች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ተናግሯል።

የኮሮናቫ ይረስ ስጋት ከአትሌቲክስ ስፖርት በተጨማሪ በአውሮፓ የሚካሄዱ የእግር ኳስ ውድድሮችን እንዲሰረዙ ወይም በዝግ ስታዲየሞቹ እንዲደረጉ አስገድዷል። በሽታው ከቻይና ባሻገር በርካታ አገራትን እያዳረሰ ሲሆን እስካሁን ድረስ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከ4366 በላይ የደረሰ ሲሆን በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ደግሞ ከ122 ሺህ በላይ መሆናቸውን እየወጡ ያሉ ዓለም ዐቀፍ መረጃዎች ያሳያሉ።

LEAVE A REPLY