የሕክምና ባለሙያዎች ሁለተኛውን ሠው ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ነፃ አደረጉ

የሕክምና ባለሙያዎች ሁለተኛውን ሠው ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ነፃ አደረጉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በለንደን ኗሪ የሆነው አዳም ካስቲሊዮ ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ነፃ መሆኑን ሕክምናውን ያደረጉለት ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው:: ግለሰቡ ከኤች አይ ቪ በተጨማሪ የካንሰር ህመምተኛ ስለነበር ለካንሰሩ የስቲም ሴል ህክምና ሲደረግለት መቆየቱ ታውቋል።

ግለሰቡ የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት መውሰድ ካቆመ አንድ ዓመት ከመንፈቅ የሞላው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ከኤች አይ ቪ ነፃ መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች አረጋግጠዋል።

የላንሴት ኤችአይቪ ጆርናል ላይ የወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው አዳም ካስቲሊዮ ዓለም ላይ በህክምና ምርምር ከኤችአይቪ መፈወስ የቻለ ሁለተኛው ሰው ሆኗል። ግለሰቡ የዳነው በፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት ሳይሆን ለካንሰር ይደረግለት በነበረው የስቲም ሴል ሕክምና እንደሆነ ታውቋል።

ለሕክምናው ስቲም ሴል የለገሱት ሰዎች ዘረ መል ባልተለመደ መልኩ ኤች አይ ቪን የመከላከል አቅም ያለው ሲሆን በዚህ የዘረ መል ባህሪ ምክንያት ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ የነበረው አዳም ካስቲሊዮም ሊፈወስ መቻሉ ተገልጿል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2011 ቲሞቲ ብራውን የተባለ የጀርመን ኤች አይ ቪ ህመምተኛ በዓለም ላይ ከኤች አይ ቪ የተፈወሰ የመጀመሪያው ሰው  በመሆን ተመዝግቦ ነበር። ተመሳሳይ የስቲም ሴል ህክምና የተደረገለትም ለሦስት ዓመት ተኩል ነበር።

የስቲም ሴል ህክምና የበሽተኞችን የበሽታ ተከላካይ ህዋሶች ኤች አይ ቪን መቋቋም በሚችሉ የለጋሾች በሽታ ተከላካይ ህዋስ በመተካት የቫይረሱን መራባት ይገታል።

የድህነት ታሪኩን በአደባባይ መናገር የመረጠው ሁለተኛው ተፈዋሽ አዳም ካስቲሊዮ 40 ዓመቱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት የኤች አይ ቪ ኢንፌክሽን በደሙ እንደሌለ ዶክተሮቹ አረጋግጠዋል። በዚህ ህክምና ላይ እየተደረገ ያለውን ምርምር የሚመሩት ፕሮፌሰር ኩማር ጉፕታ ለቢቢሲ” ይህ ውጤት ለኤችአይቪ ፈውስ እየተገኘ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው” ብለዋል። “ያገኘነው ነገር እንደሚያሳየው የስቲም ሴል ንቀለ ተከላ ለኤችአይቪ ፈውስ ነው። ይህንን የዛሬ ዘጠኝ ዓመት በበርሊኑ ታማሚ አረጋግጠናል” በማለት ይህንኑ አሰራር መከተል እንደሚያዋጣ ባለሙያዎቹ ይፋ አድርገዋል።

LEAVE A REPLY